null The Ministry of Education said that the educational road Mapping was finalized.

የትምህርት ፍኖተ ካርታ መተግበሪያ መርሃ ግብር ዝግጅት መጠናቀቁን የትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

ይህ የተገለጸው በኢፌድሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብት ልማትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የትምህርት ሚኒስቴርን የ2011 በጀት አመት ዕቅድ በገመገመበት ወቅት ነው፡፡

የትምህርት ጥራትና ተገቢነት በሚመለከት ተማሪዎች በመልካም ስነ-ምግባር የታነፁና ብቁ ዜጎችን በበቂ መጠን ማፍራት የሚያስችል፣ የመማር ማስተማር ሂደቱ ተማሪ ተኮር የሆነና በተግባር የተደገፈ፣ የምዘና፣ የፈተና እና በአጠቃላይ የጥራትና ተገቢነት ማረጋገጫ ስርዓቱ የዜጎችን የእውቀት፣ የክህሎት፣ የአመለካከት፣ የብቃትና ችሎታዎችን መመዘን የሚችል ቴክኖሎጂ የታገዘ፣ ዘመናዊ፣ ውጤታማና ቀልጣፋ እንዲሆን የሚያስችል የትምህርት ስርዓት ማጠናከርና ማስቀጠል የሚሉት በዕቅድ ውስጥ ከተካተቱት ተግባራት መካከል ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን ሚኒስቴሩን ሪፖርት ያቀረቡት አቶ እሸቱ አስፋው ገልጸዋል፡፡

የቅድመ መደበኛ ትምህርት ተሳትፎን ማሳደግና አግባብነትና ጥራቱን ማስጠበቅ፣ ጥራቱን የጠበቀ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ዕድሜያቸው ለደረሰ ሁሉ ማዳረስ፣ ገበያው የሚፈልገውን በመካከለኛና ከፍተኛ ደረጃ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት ጥራት ያለው የ2ኛ ደረጃ ትምህርትን ተሳትፎ ልዩነት በማጥበብ ፍትሐዊነትን ማረጋገጥና ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርትን በማስፋፋት የሀገሪቱን ሁለንተናዊ የልማት እንቅስቃሴ ማጠናከርን ያካተተ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

የትምህርት ፍኖተ ካርታ ዝግጅት፣ በ9ኙ ክልለሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች አጠቃላይ የኢንስፔክሽን ስራዎች፣ የፍኖተ ካርታ መተግበሪያ መርሃ ግብር ዝግጅት መጠናቀቁን፣ የትምህርት ህግ የመጀመሪያ ረቂቅ ሰነድ እና የተከለሰ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ረቂቅ ሰነድ መዘጋጀቱን አክለዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወ/ሮ እምየ ቢተው የኮሚቴውን በንኡስ ኮሚቴ የተከፈለ አዲስ አደረጃጀትና የክትትልና የቁጥጥር ስርአት አስተዋውቀዋል፡፡

የቀረበውን የዕቅድ አፈጻጸም በተመለከተም የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መሰረት ያደረገ መሆኑ፣ አጠቃላይ የትምህርት ፓኬጅን ውጤታማነት ለማሻሻል ነጥቦች ተለይተው መቀመጣቸው በጥሩ አፈጻጸም አንስተዋል፡፡

በሌላ በኩል መነሻ የሌላቸው ዕቅዶች መነሻ ሊኖራቸው እንደሚገባ፣ በጀት ከተግባራቱ ጋር ሸንሽኖ መቅረብ እንዳለበት፣ በውጭ ሀገር የሚታተሙ መማሪያ መጽሃፍትን በሚመለከት በአገር ውስጥ የሚታተሙበትን ሁኔታ ማመቻቸትና በአርብቶ አደር ክልሎች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

ከቋሚ ኮሚቴው ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ጥላዬ ጌቴ እና ሌሎች የስራ ሃላፊዎች ምላሽ የሰጡ ሲሆን በቀጣይም አስተያየቶቹን በግብአትነት በመጠቀም የተሻለ አፈጻጸም እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል፡፡