null The Ministry of Mines and Oil has decided to revise the 2019 budget plan year.

የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር የ2012 በጀት አመት ዕቅድ በድጋሚ ተሟልቶ እንዲቀርብ ተወሰነ፣

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተፈጥሮ ሀብት መስኖና ኢነርጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴርን የ2012 በጀት አመት ዕቅድ በድጋሚ ተሟልቶ እንዲቀርብ መለሰ፡፡

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተፈጥሮ ሀብት መስኖና ኢነርጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጥቅምት 27 ቀን 2012 ዓ.ም የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴርን የ2012 በጀት አመት እቅድ እና የሩብ አመት አፈጻጸም ሪፖርት ገምግሟል፡፡

የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ በተቋሙ እቅድ ላይ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት በማዕድንና ነዳጅ ዘርፍ 6 የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት የህግና የፖሊሲ ማሻሻያ ስራዎች ተካተው ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ሁለንተናዊ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በ2011 በጀት አመት ሰኔ ወር ላይ የተሰጠውን ግብረ መልስ በ2012 በጀት አመት እቅድ ላይ አለመካተቱንና የተሟላ እቅድ አለመታቀዱን አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ጀኦሎጂካል ሰርቬይ ስራ በዕቅዱ አለመካተቱን አስመልክቶ አባላቱ ጠይቀዋል፡፡

ዶክተር ሳሙኤል ከቋሚ ኮሚቴው ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት በ2ኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ባለፉት አራት አመታት ያልተሰሩ ውዝፍ ስራዎች በመኖራቸው እና በ2012 በጀት አመት ሊፈጸሙ የማይችሉ በመሆናቸው በእቅድ ያልተካተቱ መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይን በተመለከተም በዘርፉ የግብዓትና የሰለጠነ የሰው ሀይልን ጨምሮ በርካታ ክፍተቶች ያሉበት በመሆኑ ችግሮች ሳይቀረፉ በእቅድ መካተት የለበትም በሚል ታምኖበት እንደሆነ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የ2012 በጀት ዓመት እቅድ ከ2011 በጀት አመት እቅድ ጋር ሲነጻጸር ተቀንሶ የታቀደ ሲሆን የ2ኛውን እድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ያላገናዘበ መሆኑን ገልጸው እቅዱ ዋና አላማና የሚከናወኑ ዝርዝር ተግባራትን ያላካተተ ነው ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

በሌላ በኩልም ከቋሚ ኮሚቴው አባላት በዝርዝር ለተነሱ ጥያቄዎች የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አመራሮች የሰጡት ምላሽ አጥጋቢ አለመሆኑንም አባላቱ ተችተዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ ፈቲያ የሱፍ በበኩላቸው በማስፈጸም አቅም ግንባታ ስልጠና መሰጠቱን፣ በማዕድን ኢንቨስትመንት ዘርፍ ከተለያዩ አገራት ኢንቨስተሮችን ለመሳብ ስምምነት መደረጉን እና በዘርፉ የኮንትሮባንድ ንግድን ለመከላከል ነጻ የጥሪ ማዕከል መቋቋሙን በጠንካራ ጎን አንስተዋል፡፡

በአንጻሩ እቅዱ GTPውን ያላገናዘበ መሆኑን፣ ዋና አላማና ዝርዝር ተግባራት አለመቀመጣቸው፣ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮች ተለይተው በእቅዱ አለመካተታቸው፣ እንዲሁም በማዕድን ቁፋሮ የተጎዱ መሬቶች እንዲያገግሙ በደን የመሸፈን ስራ አለመከናወኑን በክፍተት ገምግመዋል፡፡

በመጨረሻም ሰብሳቢዋ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ዕቅድ ያሰራል ብሎ ቋሚ ኮሚቴው እንደማያምን ጠቁመው፤ በቋሚ ኮሚቴው የተሰጡ ግብረመልሶች የተካተቱበት የተስተካከለ እቅድ በ15 ቀናት ውስጥ ተዘጋጅቶ በድጋሚ እንዲቀርብ አሳስበዋል፡፡