null The Ministry of urban development and construction to build 48, 000 houses.

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የቤት ችግርን ለመቅረፍ በመቶ ቀናት ዕቅድ ውስጥ 48 ሺህ ቤቶች ግንባታ ለማስጀመር ማቀዱ ተገለፀ፡፡

ይህ የተገለፀው የከተማ ልማት፣ ኮንስትራክሽን እና የትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴርን የመቶ ቀናት የዕቅድ አፈጻጸም በገመገመበት ወቅት ነው፡፡

ሚኒስቴር መ/ቤቱ በመቶ ቀናት ዕቅድ ዋና ዋና የትራንስፎርሜሽን እቅድ አጀንዳዎች ከስራ እድል ፈጠራ፣ ከከተማ ልማት፣ ከቤት ልማት፣ ከኮንስትራክሽን እና ከተቀናጀ መሰረተ ልማት በተለይ ድህነት ቅነሳ አብይ ከሆኑት ጉዳዮች በመነሳት ሊለካና ውጤት ሊያመጣ በሚችል መልኩ መታቀዱን የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ጃንጥራር አባይ ገልፀዋል፡፡

ሚ/ር መ/ቤቱ በመቶ ቀናት እቅድ በፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ስራ በተመለከተ ኮርፖሬሽኑ ቤት ወደ ማልማት ስራ በስፋት እንዳልገባና አሁን ላይ እየሰራ ያለው ያሉትን ቤቶች የማከራየትና የመጠገን ስራ እንደሆነም ገልፀው ባጠቃላይ በታቀደው እቅድ መሰረትም ከ48 ሺህ ውስጥ 55ቱ ቤቶች በኮርፖሬሽኑ የሚገነቡ ሲሆኑ ቀሪዎቹ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ጨምሮ በግል አልሚ የሆኑ ሌሎች አማራጮችን በመጠቀም የሚገነቡ መሆናቸውንም ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በበኩሉ የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጭ ሊሆኑ በሚችሉ ጉዳዮችን ለአብነትም ከመሬት አስተዳደር፣ ከማዘጋጃና ከለሙ ቤቶች በተገቢው ለህብረተሰቡ ከማሰራጨት ጋር ተያይዞ ከዚህ በፊትም በህብረተሰቡ ዘንድ ቅሬታን እያስነሱ የቆዩ መሆናቸውን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት መታቀድ እንዳለበት ቢገለጽም ሚ/ር መ/ቤቱ በበኩሉ አሁን ላይ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመስራት የተነሱ ቅሬታዎችን ሊፈቱ በሚቻል ደረጃ ላይ መድረሱን አብራርቷል፡፡

ሚ/ር መ/ቤቱ በትራንስፎርሜሽን እቅድ ውስጥ ድህነትን ለመቀነስ ግንባር ቀደም ተደርጎ የተያዘው የስራ ዕድል ፈጠራ በተመለከተ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከታቀደው አንጻር ሲታይ አፈጻጸሙ ዝቅተኛ ከመሆኑም ባሻገር ከተጠሪ ተቋማት ጋር ያለው እቅድ ያልተጣጣመ በመሆኑ ታይቶ መከለስ እንዳበትም ቋሚ ኮሚቴው በግምገማው አንስቷል፡፡

ቋሚ ኮሚቴ ሚ/ር መ/ቤቱ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ሲታይ ባለፉት ዓመታት ሰፊ የአቅም ግንባታ ጉድለቶች የነበሩበት ዘርፍ መሆኑን አስታውሶ ጉድለቶችን በመሙላት ቀጣይ ህዝብንና መንግስት ከዘርፉ የሚጠብቁትን ውጤቶች ምን እንደሆኑ ጠይቋል፡፡

የኮንስትራክሽን ስራ በባህሪው ውስብስብና አስቸጋሪ በመሆኑ ሊያሰሩ የሚችሉ መመሪያዎችን በመዘርጋት ክፍተት ያለባቸውን አማካሪዎችንና ኮንትራክተሮችን በመለየት እንዲሁም ስልጠናዎችን በመስጠት ላይ እንደሆኑ በሚ/ር መ/ቤቱ በኩሉ ተጠቁሞ፤ ዘርፉ የተሳካለት ውጤት እንዲያመጣ ከተፈለገ ሁሉም ባለድርሻ አካለት እገዛ እንደሚያስፈለግ ጠቁመዋል፡፡