null The Ministry of Urban Development and Housing noted that it would need to coordinate with stakeholders to address the limited implementation constraints in the construction of housing and caterers.

የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር በመኖሪያ ቤቶች ግንባታና ካዳስተር ዙሪያ የሚታይበትን የአፈጻጸም ውስንነት ለመቅረፍ  ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት እንዳለበት ተመለከተ፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን የ2010 ዓ/ም በጀት አመት አጠቃላይ አፈጻጸምና የቀጣይ 2011 ዓ.ም በጀት አመት መነሻ እቅድ ላይ ተወያይቷል፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መካከለኛ አመራሩ ለመልካም አስተዳደር ችግሮች ፖለቲካዊ ፋይዳና ትርጉም ተገንዝቦ መምራት አለመቻሉ፣ ፈጻሚው በቁርጠኝነት ከመስራት አንጻር ውስንነት መኖሩ፣ በአመራሩም ሆነ በፈጻሚው ዘንድ በጊዜ የለኝም መንፈስ የመስራት ልምድ ውስንነት፣ ፈጻሚው በተመደበበት የስራ መስክ ላይ የእውቀት ክፍተት መኖሩን በእቅድ አፈጻጸሙ ወቅት የተከሰቱ ውስንቶች መሆናቸውን የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የስራ ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡

ሚኒስቴር መ/ቤቱ በ2011 ዓ.ም ሃገር አቀፍ የሞዴል ከተሞች ደረጃ (ስታንዳርድ) እንደሚዘጋጅ፣ 66,000 ለሚሆኑ ሰነድ አልባ ይዞታዎች ሰነድ እንደሚሰጥ፣ በ11 ከተሞች ዘመናዊ የመሬት ግብይት ማዕከላት እንደሚቋቋሙ እንዲሁም በአምስት የክልል እና በድሬዳዋ ከተማ የመሬት ተቋማት ህንጻ እንዲጠናቀቁ ካቀዳቸው እቅዶች መካከል ይገኙበታል፡፡

የእቅድ ዝግጅቱ አመለካከትን፣ ክህሎትንና እውቀትን መነሻ ባደረገ መልኩ መዘጋጀቱ፣ በእድገትና ትራንስፎርሜሽኑ የተቀመጡ ዋና ዋና ግቦች ከፖሊሲና ስትራቴጂ የመነጩ መሆናቸውን፣ እቅዱ ስትራቴጂካዊ ግቦችን መሰረት አድረጎ መታቀዱ፣ ስጋቶችንና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ያካተተ መሆኑን ቋሚ ኮሚቴው በጥንካሬ ከጠቀሳቸው መካከል ይገኙበታል፡፡

በሌላ በኩል የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮችን ለመፍታት በዝርዝር አካቶ አለማቀድ፣ በዕቅድ ውስጥ የተቀመጡ ግቦች በቁጥር አናሳ መሆን፣ በስራ እድል ፈጠራ ዙሪያ በበቂ ሁኔታ አለመታቀዱን እንዲሁም መኖሪያ ቤት ግንባታና ካዳስተር ስራዎች ላይ ውስንነት መኖሩን ቋሚ ኮሚቴው በእጥረት ለይቷል፡፡

በመጨረሻም የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ፉፊ ድልጋሳ የህብረተሰቡን የመኖሪያ ቤት ችግር እንዲሁም ከዚያ ጋር ተያይዞ የሚነሳውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመቅረፍ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አጽኖት ሰጥቶ ውስጣዊ አሰራሩን በመፈተሸ መስራት እንደሚኖርበት አሳስበዋል፡፡

የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር ሚንስትር አቶ ጃንጥራር አባይ በበኩላቸው ከመኖሪያ ቤት ግንባታ እና ከካዳስተር ስራዎች ጋር በተያዘዘ ውስንነት መኖሩን ተቀብለዋል፡፡ ችግሩን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ብቻውን ሊፈታው የሚችል እንዳልሆነ ጠቁመው በቋሚ ኮሚቴው በኩል አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደረግላቸውም ጠይቀዋል፡፡