null The nation's debt collection is on risky condition.

  የሃገሪቱ እዳ ክምችት አሳሳቢ እንደሆነ ተገለጸ፡፡

ግንቦት 28 ቀን 2011 ዓ.ም ፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአራተኛ አመት የስራ ዘመኑ በስድስተኛ ልዩ ስብሰባው የገንዘብ ሚኒስቴርን የ 2011 ዓ.ም በጀት አመት የአስር ወራት አቅድ አፈጻጸም ሪፖርት አዳምጧል፡፡

የሃገሪቱ እዳ ክምችት ከኤክስፖርት አፈጻጸሙ ጋር ሲነጻጸር አሳሳቢ መሆኑን የገንዝብ ሚኒስቴር ሚስትሩ  አቶ አህመድ ሽዴ የመስሪያ ቤታቸውን የአስር ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት  ባቀረቡበት ወቅት ተናግረዋል፡፡

የኤክስፖርት አፈጻጸም ውስንነትን  በዘላቂነት ለመፍታት የግል ሴክተሩን  በከፍተኛ ደረጃ በማሳተፍና አላሰራ ያሉ  ማነቆዎችን ለይቶ በመንቀሳቀስ  ኤክስፖርት ተኮር ስራዎችን  መስራት እንደሚገባም አቶ አህመድ ገልጸዋል፡፡

የኤክስፖርቱ ገቢ  አፈጻጸም  ከአመት አመት ማሽቆልቆል የማክሮ ኢኮኖሚው ጤናማ አለመሆን መገለጫ መሆኑን ያነሱት አቶ አህመድ ፤ የኢኮኖሚ ሚዛን ክፍተቶችን ለመሸፈን በከፍተኛ ሁኔታ እየተሰራ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡

በ2011 በጀት አመት አስር ወራት ውስጥ ከኤክስፖርት 2.1 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ቢገኝም ከ 2010 በጀት አመት ተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው 2.3 ቢሊዮን ዶላር ጋር ሲነጻጸር በ 187.1 ሚሊዮን ዶላር ቅናሽ ማሳየቱን አቶ አህመድ ገልጸዋል፡፡

በማዕከላዊሰ ስታቲስቲክስ  ኤጀንሲ መሰረት በሚያዚያ ወር 2011 ዓ.ም የአስራ ሁለት ወራት ተንከባላይ አማካይ ሃገራዊ አጠቃላይ የፍጆታ እቃዎች ዋጋ እድገት 12.6 በመቶ መሆኑንም አቶ አህመድ ጠቅሰዋል፡፡

የዋጋ ንረቱ በአንድ አሃዝ እንዲገደብ ለማድረግ ያልተቻለ ቢሆንም በዝቅተኛው የሁለት አሃዝ እንዲረጋጋ ለማድረግ እንደተቻለም ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡

በዋናነት ለዋጋ ንረቱ የአቅርቦት ችግር ፤ ውስጣዊ የፖለቲካ አለመረጋጋትና የህግ የበላይነት አለመከበር ምክንያቶች እንደሆኑ አቶ አህመድ ተናግረዋል፡፡

የውጭ ክፍያ ሚዛን መዛባት ለማክሮ ኢኮኖሚው አለመረጋጋት ከሚጠቁሙት የኢኮኖሚ መሳሪያዎች ውስጥ አንዱ መሆኑን የጠቀሱት አቶ አህመድ ፤ ለሃገራችን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አስፈላጊ የሆኑ ሸቀጦችንም ሆነ የካፒታል እቃዎች በሃገር ውስጥ  ማሟላት እንዳልተቻለና ከውጭ ማስገባት ግዴታ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

 የውጭ ምንዛሬ አቅርቦታችን አስተማማን ምንጭ የሆነው የሸቀጦች የውጭ ንግድ አፈጻጸም ችግር እንደገጠመው ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡

የኢኮኖሚ ሚዛንን በመጠበቅ የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን ለመፍጠር በተደረገው ጥረት ባለፉት አስር ወራት የመንግስትን ወጪ በገቢው እንዲሸፈንና የእዳ ጫናን ለማቃለል የሚያስችሉ ተግባራት እንደተከናዎኑ  አቶ አህመድ ተናግረዋል፡፡

 በኢኮኖሚው ውስጥ እድገት ቢኖርም የእድገት ፍጥነቱ  ግን እየቀነሰ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በ2011 ዓ.ም በጀት አመት እሰበስባለው ብሎ ካቀደው ብር  235.7 ቢሊዮን ውስጥ 160.4 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ እንደተቻለም ሚኒስትሩ አክለዋል፡፡

የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ እስካሁን ደንብና መመሪያ አልወጣለትምና አፈጻጸሙ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ  ከምክር ቤት አባላት ጥያቄ ተነስቶላቸዋል፡፡

 ገንዘቡን የሚያስተዳድሩት ክልሎች ስለሆኑ የተዘዋዋሪ ፈንዱ አፈጻጸም በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ  የተጠቃለለ ሪፖርት እንዳልደረሳቸውና  መመሪያና ደንብም በቅርብ እንደሚወጣለት  ተናግረዋል፡፡

የሃገራችን የውጭ እዳ ክፍያን ለማቃለል ከቻይና ጋር የተደረጉ የዲፕሎማሲ ስራዎች ውጤታማ መሆናቸው ፤ 188 የፌደራል ባለበጀት መስሪ ቤቶች  ኦዲት ሪርት እንዲመረመር መደረጉን ቋሚ ኮሚቴው በጥንካሬ ከጠቀሳቸው መካከል ናቸው፡፡

በሌላ በኩል የውጭ እዳ ክፍያ አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆኑና ሴቶችን ወደ አመራርነት ለማምጣት በቂ ስራ እየተሰራ አለመሆኑን ቋሚ ኮሚቴው በእጥረት አንስቷል፡፡

ምክር ቤቱ ዶ.ር ንጉሴ ምትኩ ገላው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆነው እንዲሾሙ በኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ.ር ዐቢይ አህመድ  የቀረበለትን ሹመት  በአብላጫ ድምጽና በአራት ድምጸ ተዓቅቦ አጽድቆታል፡፡

ዋና ስራ አስፈጻሚውም በምክር ቤቱ ፊት ቀርበው ቃለ- መሃላ ፈጽመዋል፡፡

አንድ የምክር ቤት አባል የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ዋና ስራ አስፈጻሚ ከስራቸው የለቀቁበት ምክንያት  እንዲገለጽላቸው ሹመቱን ያቀረቡትን የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነትን  ቢጠይቁም የቀድሞው ዋና ስራ አስፈጻሚ የለቀቁበትን ምክንያት ቋሚ ኮሚቴው  ያውቀዋል፤ በገዛ ፈቃዳቸው ስራቸውን እንደለቀቁ ሰምተናል  በማለት ሁኔታውን  በዝርዝር ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡