null The National Animals Genetics Improvement Institute should focus to solve the challenges facing.

የብሔራዊ የእንሰሳት ዝርያ ማሻሻያ ኢንስቲትዩት ያሉበትን ችግሮች በመፍታት የሚጠበቅበትን ውጤት ለማምጣት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት የግብርና፣ አርብቶ አደርና አካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡

ጥር 13 ቀን 2011 ዓ.ም ቋሚ ኮሚቴው የብሔራዊ የእንሰሳት ዝርያ ማሻሻያ ኢንስቲትዩት የ2011 ዓ.ም የግማሽ አመት የዕቅድ አፈጻጸም ገምግሟል፡፡

የብሔራዊ የእንሰሳት ዝርያ ማሻሻያ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶ/ር ኢሳያስ ተሰማ  በግማሽ አመቱ ውስጥ የህብረተሰብ ተሳትፎን በሚመለከት በዳልጋ ከብት ወተት ዝርያ ማሻሻል ከታቀደው በላይ መከናወኑንበዳልጋ ሥጋ ከብት 34%፣ በበግና ፍየል ዝርያ ማሻሻል የዕቅዱ 7% ያህል ማሳተፋቸውን ገልፀዋል፡፡  

በማዕከሉና በክልሎች 602,000 ዶዝ አባለዘር ለማሰራጨት ታቅዶ 544,353 ዶዝ የዕቅዱን 90% እንደሆነና ይህ ስርጭት በክልሎች እና በማዕከሉ የተሰራጨውን ያካተተ ሲሆን ከግማሽ ዓመቱ ስርጭት ውስጥ 499,998 ዶዝ በፌደራሉ ማዕከል የተሰራጨ ሲሆን ቀሪው 44,355 ደግሞ በክልሎች የተሰራጨ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የፈሳሽ ናይትሮጂን ምርትን በተመለከተ በግማሽ ዓመቱ ውስጥ በማዕከሉና በክልሎች 260,000 ሊትር ለማምረት ታቅዶ 173,091 ሊትር የዕቅዱን 67% መሆኑን ይህ ምርት በክልሎች እና በማዕከሉ የተመረተውን ያካተተ ሲሆን ከግማሽ ዓመቱ ምርት ውስጥ 143,620 ሊትር በክልሎች የተመረተ እንደሆነና ቀሪው 29,471 ሊትር በፌደራሉ ማዕከል የተመረተ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

50 አዳቃይ ቴክኒሻኖችን ለማሰልጠን ታቅዶ 42 መሰልጠናቸውን፣ ዝርያቸው በመመናመን ላይ ያሉ የሼኮ እና የኢሮብ ዝርያዎችን ለመጠበቅ የተሰበሰበ ዶዝ አባላዘር በሚመለከት ከዕቅዱ ሃያ ስምንት በመቶ መከናወኑን አብራርተዋል፡፡

አባለዘር አምራች የሆኑ ታዳጊ ኮርማዎችን በሚፈለገው መጠን ማግኘት አለመቻል፣ በውጭ ምንዛሬ እጦት ምክንያት ለአባለዘር ምርት የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ማግኘት አለመቻልከፍተኛ ባለሙያዎች በገበያ ላይ አለመገኘትና ኢንስቲትዩቱ በአግባቡ አለመደራጀቱ በግማሽ አመቱ ያጋጠሙዋቸው ችገሮች እንደሆኑና ለአፈጻጸሙ ዝቅተኛ መሆን ምክንያቶች መሆናቸውን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ተቋሙ የአባላዘር ስርጭት ላይ ብቻ የተሻለ ስራ መስራቱን ገልጾ አጠቃላይ አፈጻጸሙ ዝቅተኛ ሆኖ የበጀት አጠቃቀሙ ከፍ ማለት፣ ታቅደው ያልተከናወኑ በርካታ ተግባራት መኖራቸው፣ የ1ለ5 አደረጃጀት ውጤታማ አለመሆን፣ የእንሰሳት ዝርያ ማሻሻል  ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ገልጿል፡፡

አጠቃላይ የአበይት ተግባራት አፈጻጸም ዝቅተኛ በመሆኑ ከዚህ ዝቅተኛ አፈጻጸም ለመውጣት በቀጣይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል፡፡ በመጨረሻም የተቋሙን አደረጃጀት በሚመለከት ያሉ ክፍተቶችን ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር እንደሚወያይበት ገልጿል፡፡