null The prisoners said that, the pardon given by the government did not include us.

መንግስት ለታራሚዎች ያደረገው ይቅርታና ምህርት እኛን አላካተተም ሲሉ በቅሊንጦ ማረሚ ቤት የሚገኙ ታራሚዎች ቅሬታቸውን አሰሙ፡፡

ታራሚዎቹ ቅሬታቸውን ያቀረቡት ሰሞኑን በህዝብ ተዋካዮች ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌደራል ማረሚያ ቤቶችን የአካል ምልከታ በአደረገበት ወቅት ሲሆን መንግስት ለውጡን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስና የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስረፋት አቅዶ እየሰራ ቢሆንም ተደረገው ይቅርታና ምህረት ፖለቲከኞችና ታዋቂ ግለሰቦች ላይ ያተኮረ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

አቶ ሰለሞን ገነቱ በቅሊንጦ የዞን አንድ ጣቢያ ታራሚ ሲሆን በፌደራል ማረሚያ ቤቶች ከ1ሺ ለማይበልጡ ታራሚዎች ምህረት መሰጠቱ ባይካድም ማረሚያ ቤቱ ለውሳኔው ተፈጻሚነት ያለው ቁርጠኝነት እጅግ ዝቅተኛ በመሆኑ በይቅርታው መካተት ያለባቸው ታራሚዎች እስካሁን እድሉን ማግኘት ያልቻሉ በመሆኑ መንግስት ያስተላለፈው መመሪያ መፈጸም አለመፈጸሙን ተከታትሎ ሊያረጋግጥና የመፍታት እድሉን ያላገኘን ታራሚዎች ትኩረት ሊሰጠን ይገባል ብሏል፡፡

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሽብር አዋጁን ጨምሮ ሌሎች ፍትሃዊነት የጎደላቸው የወንጀል ህጎች እንዲሻሻሉና ከሁሉም ወገን የተወጣጡ አማካሪዎች ተካትተውበት የማሻሻያ ሀሳብ ለምክር ቤቱ መቅረብ አለበት  ሲል ለቋሚ ኮሚቴው አቤቱታ አቅርቧል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ከታራሚ ተወካዮች ጋር ባካሄደው በውይይት ለታራሚዎች የሚሰጠው የፍትህ አገልግሎት አነስተኛ መሆኑን፣ በቡራዩ ከተማ የተመደቡ ፖሊሶች የስነ-ምግባር ችግር ያለባቸው መሆኑንና በቂሊንጦ የቀጠሮ ማረሚያ ቤት ከ3 እስከ 5 ዓመት ያለምንም ፍርድ የታሰሩ ታራሚዎች መኖራቸውንና መንግስት ሊፈትሸው እንደሚገባ አሳስበው ከአዲስ አበባ ከተማ ታፍሰው የታሰሩ ዜጎችን መንግስት ችላ እንዳላቸውና የውሸት ምስክር ተሰምቶባቸው እንደታሰሩም ለቋሚ ኮቴው ተቁመዋል፡፡

እንደታራሚዎቹ ገለጻ በአሁኑ ወቅት በቀጠሮ ማረሚ ቤቱ ምንም አይነት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሌለና የተሻለ አገልግሎት እንደሚያገኙ ጠቅሰው አልፎ አልፎ ግን ዘመድ የሚያቀርብላቸውን ምግብ ለማስገባት እንደሚቸገሩና አድልዎ እንደሚፈጸምባቸው በዝርዝር አስረድተዋል፡፡

የቀጠሮ ማረሚያ ቤቱ ዋና አስተዳዳሪ ጫላ ጸጋ በታራሚው ላይ ያለውን መሰረታዊ ችግር በተለይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ ማረሚያ ቤቶች ከመንገስት የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ፣ ያለውን ቅንጅታዊ አሰራር እንዲሁም ከታራሚው ምግብና ጽዳት አያያዝ አኳያ ያለው ሁኔታ የተሻለ እንደሆነ ለቋሚ ኮሚቴው አስረድተዋል፡፡

አቶ ጫላ አክለውም በቀጠሮ ማረሚያ ቤቱ ታራሚዎችን ወደ ተለያዩ ፍርድ ቤቶች ለማመላለስ የተሸከርካሪ (የአንቡላንስ) ችግር፤የመብራት መቆራረጥና አብዛኘው ታራሚ የስነ-ምግባር ችግር እንዳለበትና የፖሊስ አባላትን አሳሪና ፈች አድርጎ በመቁጠር መብትና ግዴታውን ጠብቆ እያታረመ  አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በበኩሉ የታራሚዎች የሰብዓዊ መብት አያያዝ ጥሩ እንደሆነና የተቋሙ አመራር ኃላፊነቱን በተገቢው እየተወጣ እንዳለ ገልጾ በማረሚያ ቤቱ ውስጥ አለ እየተባለው ጨለማ ቤት በቀጣይ የሚጣራ መሆኑን አስረድቷል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው አክሎም በማረሚያ ቤት የህግ የበላይነት ሊረጋገጥና የመረጃ አያያዙም መዘመናዊ ሊሆን እንደሚገባ እንዲሁም ታራሚዎችን በወንጀላቸው ለይቶ ማስቀመጥ፣ ለረጅም አመት ፍርድ ላላገኙ ተጠርጣሪዎች ውሳኔ መስጠትና የታራሚዎችን ስርዓት አልበኝነት ጉዳይ ከስር መሰረቱ በመፍታት በማረሚያ ቤቱ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ይገባል ሲል ቋሚ አሳስቧል፡፡