null Second Africa-Turkey Ministerial Review Conference

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት  ተቋቁሞ  በግጭቱ  ወደ ተፈናቀሉ  ዜጎች  የተሰማራው የሱፐርቪዥን ቡድን ያዘጋጀውን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ ለምክር ቤቱ ያቀረበ ሲሆን ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል፤የምክር ቤት አባላት ላነሷቸው ጥያቄዎችም የአስተባባሪው ኮሚቴ አባላትና የሱፐርቪዥን ቡድኑ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የሁለቱ ክልል ህዝቦች ለዘመናት ተከባብረው፣ ተፋቅረውና ተዋልደው በኖሩት አከባቢ በተፈጠረው ግጭት የሰው ህይወት መጥፋቱንና ዜጎች ለረጅም ዓመታት ያፈሩት ንብረታቸው መውደሙን  ሪፖርቱ አመላክቷል። ፡፡

ህገ-መንግስቱ ማንኛውም ዜጋ በመረጠበት ቦታ የመዘዋወር፣ የመኖርና ሀብትና ንብረት የማፍራት መብት ያጎናፀፈ በመሆኑ ከሁለቱም ክልል የተፈናቀሉ ዜጎችም ወደ ነበሩበት ቦታ እንዲመለሱ ዘርፈ-ብዙ ድጋፍ እንዲደረግላቸው፣ ወደ ቦታቸው የማይመለሱትን ዜጎች የፌደራልና የክልል መንግስታት ድጋፍ በመስጠት በአስቸኳይ የማቋቋምና ወደ ተረጋጋ ኑሮ የመመለሱ ስራ መፋጠን እንዳለበት የሱፐር ቪዥኑ ቡድን አስተባባሪ አቶ ጫኔ ሽመካ ገልጸዋል፡፡

የግጭቱ መነሻ በህዝቦች መካከል የተፈጠረ አለመሆኑ ከሁለቱም ክልል ተፈናቃይ ዜጎች በተሰጠ አስተያየት መረዳት የተቻለ ሲሆን፣ ለዜጎች መፈናቀልና ህይወት መጥፋት መንስኤው ህዝቡ ሳይሆን መሬትን መሰረት ያደረገ የኪራይ ሰብሳቢው ፍላጎትና ያለአግባብ ልጠቀም የሚል አጀንዳ እና በ1997 ዓ.ም የተካሄደውን ህዝበ ውሳኔ መሰረት አድርጎ የሁለቱ ክልሎች የወሰን ማካለል ስራውና የህግ የበላይነትን የማስከበር ተግባሩ በወቅቱ አለመፈጸም ግጭቱን እንዳባበሰው ተገልጿል፡፡

በውይይቱም ግጭቱ በተነሳበት ወቅት መንግስት አፋጣኝ ርምጃ ከመውሰድ ለምን እንደተቆጠበ፣ የሱፐርቪዥኑ ሪፖርት መዘግየቱንና ግጭቱ የተከሰተባቸውን ሁሉንም ቦታዎች የዳሰሰ አለመሆኑ የምክር ቤት አባላት ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡