null The various problems at Kalliti prison should be solved urgently.

በቃሊቲ ማረሚያ ቤት የሚስተዋሉ ዘርፈ-ብዙ ችግሮች በአፋጣኝ ሊፈቱ ይገባል ሲል የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፣    

ቋሚ ኮሚቴው ሰሞኑን በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ባደረገው የመስክ ምልከታ የማረሚያ ቤቱን የህክምና ክፍሎች፣የታራሚ ማረፊያ ቤቶችና መሰረተ-ልማቶችን ተዘዋውሮ ተመልክቷል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ታራሚዎችን እና የማረሚያ ቤቱን አስተዳደር ሰራተኞች ባወያየበት ወቅት ማረሚያ ቤቱ ታራሚዎችን በማረምና በማነጽ ደረጃ ላይ አለመሆኑን፤የፍትህ መጓተት መስተዋሉንና በህግ እየተዳኙ አለመሆኑን ያነሱት ታራሚዎቹ መንግስት በ2010 ዓ/ም ባደረገው ይቅርታ እኛ ተጠቃሚ አይደለንምና ይቅርታ ሊያደርግለን ይገባል ሲሉ ሃሳባቸውን ገልጸዋል፡፡

የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር ሰራተኞች እና የፖሊስ ጥበቃ አባላት በበኩላቸው በማረሚያ ቤቱ ብዙ ችግሮች እንዳሉ በዝረዝር የገለጹ ሲሆን በዋናነትም ሚዲያው በህግ ታራሚ ዜጎች ላይ አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸሙን በቂ መረጃ ሳይዝ ሚዛናዊ ባልሆነ መንገድ  በመዘገቡ በማረሚያ ቤቱ ገጽታ ላይ ካሳደረው ተጽእኖ ባሻገር በሰራተኞች ላይም ክፍተኛ የሞራል ኪሳራ ማድረሱን ተናግረዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህም በታራሚዎች ስድብና ዛቻ እየደረሰባቸው እንደሆነ የገለጹት የማረሚያ ቤቱ ሰራተኞች በሚዲያ የተሰራጨው ዘገባ በማህበራዊ ኑሯቸውም ላይ ተጽእኖ በማሳደሩ ስራቸውን በመሸማቀቅና በመሰላቸት እንደሚያከናውኑ ነው የተናገሩት፡፡

በሌላ በኩል የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር የደመወዝ አከፋፈል ስርዓት የሰራተኛውን ልምድና ብቃት ያገናዘበ አለመሆኑን፣ማግኘት የነበረባቸውን ጥቅማጥቅም እንደማያገኙና ያገለገሉበትን የስራ ልምድ ሲጠይቁ የማይሰጣቸው መሆኑን በምሬት ገልጸው ማረሚያ ቤቱ በቂ መሰረተ-ልማቶች ስላልተሟሉለት ለታራሚም ሆነ ለማረሚያ ቤቱ ሰራተኞች ምቹ እንዳልሆነም አያይዘው ተናግረዋል፡፡   

በማረሚያ ቤቱ ዘርፈ-ብዙ ችግሮች እንዳሉ ማረጋገጣቸውን የተናገሩት የቋሚ ኮሚቴው አባላት እንዳሉት በቀጥታ በዚህ ማረሚያ ቤት ውስጥ ባይሆንም በዜጎች ላይ አሰቃቂ የሰብአዊ መብት ጥሰት መፈጸሙንና በቀጣይ ትክክለኛ  መረጃ ሲገኝ በህግ ተጠያቂ የሚሆን አካል ይኖራል ብለዋል፡፡

ማረሚያ ቤቱ ታራሚዎችን የማረምና የማነጽ ተልዕኮ ቢኖረውም፣ትኩረት የያደርገው ማረም ላይ ብቻ እንደሆነና ታራሚዎች ለሚሰሩት ስራ የገቢያ ትስስር አለመፍጠሩን የተመለከተው ቋሚ ኮሚቴው በቀጣይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብሏል፡፡

የይቅርታ አሰጣጥ ላይ በግልጽነትና የአስተምህሮ ስራ በሰፊው ባለመሰራቱ በታራሚዎች ላይ የግንዛቤ ክፍተት የሚስተዋል መሆኑን የጠቆመው ቋሚ ኮሚቴው በማረሚያ ቤቱ ለታራሚዎች በሀኪም የሚታዘዙ መድሀኒቶች በቀላሉ አለመገኘት፣ የአምቡላስ እጥረት፣ የፍትህ መጓተትና የሀሰት ምስክር መበራከት ማረሚያ ቤቱ ለታራሚዎች ምቹ እንዳይሆን ያደረጉት በመሆኑ ሊስተካከል ይገባል ብሏል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው አክሎም ፍርድ ቤት፣አቃቤ ህግና ማረሚያ ቤቱ በቅንጅት ከመስራት አኳያ ክፍተት መኖሩንና አደንዛዥ እጽ ወደ ማረሚያ ቤት እንዳይገባ የሚደረገው ቁጥጥር ትኩረት የሚሻው መሆኑን አሳስቦ ማረሚያ ቤቱ ለህዝብ ክፍት መሆኑን ሴቶችንና ልዩ ድጋፍ የሚሹ ታራሚዎችን ለመንከባከብ የሚደረገውን ጥረት በጠንካራ ጎን አንስቷል፡፡