null Tourism and culture in Benishangul improperly promoted: House

በቤኒሻንጉል ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በመተከል ዞን የሚገኙት የባህልና የቱሪዝም መስህቦችን በአግባቡ የማልማትና የማስተዋወቅ ስራ አለመሰራቱ ተገለፀ፡፡

ይህ የተጠቆመው የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በክልሉ መተከል ዞን ማንዱራ ወረዳ የሚገኙትን የባህልና የቱሪዝም መስዕቦችን አስመልክቶ ባደረገው የመስክ ምልከታ ወቅት ነው፡፡

በጉብኝቱም የወረዳው የኮሚዩኒኬሽንና ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ ሌንሳ ሞሲሳ በወረዳው በተለይ የጉምዝ ብሄረሰብን የሚገልፅ አንድ አነስተኛ የባህላዊ ቅርሶች ማሳያ ሙዚየም፣ በተለያዩ ማህበራዊ ክንውኖች እና በዓላት ላይ በመገኘት ባህላዊ ትርኢት የሚያቀርቡ 2 የባህል ቡድኖች፣ ጃሚካ በመባል የሚጠራና የስነ-ዕሁፍ ምሽት በማዘጋጀት የብሄረሰቡን ባህልና እሴት የሚያስተዋውቅ ክበብ፣ በማረሚያ ቤት የሚሰሩ ልዩ ልዩ የዕደ ጥበብ ስራዎች፣ ታሪካዊ ዋሻዎችን እና አንድ ፓርክን ጨምሮ 4 የቱሪዝም መስዕብ ስፍራዎች መኖራቸውን አብራርተዋል፡፡

ይሁን እንጂ ወደ 4ቱ የቱሪዝም መስዕብ ስፍራዎች የሚያደርስ የመንገድ መሰረተ ልማት እና ስራውን በአግባቡ ለማከናወን የሚያስችል በጀት ባለመኖሩ ወረዳው ከዘርፉ ማግኘት የሚገባውን ጥቅም እንዳያገኝ አድርጎታልም ብለዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ቡድን አባላት የማንዱራ ወረዳ ሚኒ ሚዚየምን በጎበኙበት ወቅት በወረዳው የሚገኘውን የጉምዝ ብሄረሰብ ማንነትና ባህል የሚያሳዩ ልዩ ልዩ ቁሳቁሶች በሚዚየሙ ተሰባስበው መገኘታቸውንና በወረዳው የሚገኙ የቱሪዝም መስዕብ ስፍራዎችን መለየት መቻላቸውን በጥንካሬ አንስቷል፡፡

በሌላ በኩል ተፈጥሯዊ መስህቦችን እና የብሔረሰቦችን ባህል በማልማትና በማስተዋወቅ በኩል በቂ ስራዎች አለመሰራታቸው በእጥረት አስቀምጧል፡፡

ዞን ወደ ታላቁ የህዳሴ ግድብና ስኳር ፕሮጀክት መሄጃ ኮሊደር ላይ የሚገኝ በመሆኑ በዘርፉ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግና ተገቢውን ጥቅም ለማግኘት ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባም ነው የቡድኑ አባላት ያመለከቱት፡፡

ዘጋቢ:- ሀይለሚካኤል አረጋኸኝ