null Trade and Industry affairs standing committee urged the industry parks to improve export trade.

የኢንዱስትሪ ፓርክ ኮርፖሬሽን የሚስተዋልበትን የአፈጻጸም ችግሮች በመቅረፍ የኤክስፖርት አቅሙን ማሳደግ እንደሚገባው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በኮርፖሬሽኑ የአምስት ወራት እቅድ አፈጻጸም ዙሪያ ተወያይቷል፡፡

በአንዳንድ ፓርኮች ላይ ኮርፖሬሽኑ ውጤታማ የኤክስፖርት አፈጻጸም ቢኖረውም እንደ አጠቃላይ የአምስት ወራት እቅድ አፈጻጸሙ ሲገመገም ግን ውጤቱ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ጌታቸው መለሰ ተናግረዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ የኤክስፖርት አቅሙን ለማሳደግና እንቅፋት የሆኑበትን ችግሮች ለመፍታት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በተደራጀ መልኩ ውይይት ማድረግ እንዳለበትም አቶ ጌታቸው አክለዋል፡፡

ፈጻሚን ማዘጋጀትና የሰው ሃይል ማሟላት መቻሉ፣ በእቅድ የተያዙ ስልጠናዎች መርሃ-ግብራቸውን ጠብቀው መከናወናቸው፣ ቦሌ ለሚ ፓርክ ላይ በቂ የውሃ አቅርቦት መኖሩ፣ የቦሌ ለሚ ላይ ውጤታማ ኤክስፖርት ምርት መደረጉ፣ ሃዋሳና ቦሌ ለሚ ላይ አመርቂ የስራ እድል መፈጠር መቻሉን ቋሚ ኮሚቴው በጥንካሬ ከጠቀሳቸው መካከል ይገኙበታል፡፡

በሌላ በኩል የትኩረት መስክ ተግባራት በግልጽ አለመቀመጣቸውን፣ የመልካም አስተዳደር  ሪፖርት አለመላኩን፣ ነባር ፓርኮችን አለማጠናቀቅ፣ እንደ አጠቃላይ በቂ የስራ እድል አለመፈጠሩን እና የአንድ ማዕከል አገልግሎት በተጠናከረ ሁኔታ አለመቀጠሉን ቋሚ ኮሚቴው ትኩረት የሚሻቸው ጉዳዮች ናቸው ሲል ጠቅሷል፡፡

የኮርፖሬሽኑ የስራ ኃላፊዎች በበኩላቸው ለአፈጻጸሙ ዝቅተኛ መሆን በቂ የሃይልና ውሃ አቅርቦት አለመኖር፣ ከፍተኛ የፋብሪካ ሰራተኞች ፍልሰት መኖሩ፣ የቴሌኮም አገልግሎት አዝጋሚነት እንዲሁም የፓርክ አገናኝ መንገዶች ውስንነት መኖሩን ገልጸው፤ በቋሚ ኮሚቴው በኩል ትኩረት ይሻቸዋል ተብለው በአስተያየት የተዘረዘሩ ነጥቦችን በግብዓትነት ወስደው በቀጣይ ውጤታማ ስራ እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡