null Urgent legal actions should be taken against Leaders and security forces with upper hands on the displacement of citizens.

በአገሪቱ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ለተከሰተው መፈናቀል ዋናውን ሚና የተጫወቱ በየደረጃው ያሉት የአመራርና አንዳንድ የጸጥታ አካላት ላይ ተገቢውን ማጣራት ተደርጎ በህግ ፊት የማቅረብ ስራ ሊሰራ እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረገው 5ኛ ልዩ ስብሰባ ተገለፀ፡፡

በልዩ ስብሰባውም ም/ቤቱ የቀድሞ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ክቡር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ የቀብር ስነ ስርዓት አፈጻጸምን አስመልክቶ የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡

ከሁሉም ቋሚ ኮሚቴ የተወጣጡ የክትትል ቡድን አባላት በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች በተከሰተው ግጭት የተፈናቀሉት ዜጎች ያሉበትን ሁኔታ በማየት የሚያቀርበውን ሪፖርት አድምጦ የህግ፣ ፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴው ያቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ በምክር ቤቱ መርምሮ በሁለት ተቃውሞ በአራት ድምጸ ታቅቦ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል፡፡

በወቅቱም በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች የበርካታ ዜጎች ህይወት መጥፋት፣ የአካል ጉዳት፣ ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀል አደጋ ያጋጠማቸው ሲሆን መፈናቀላቸውን ተከትሎ የተለያዩ የሰብዓዊ ድጋፍ የማድረግና መልሶ የማቋቋም ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ በተገኘውም መረጃ መሰረት አጠቃላይ በትግራይ ክልል 111 ሺህ 465፣ ከበቡብ ብሔር ብሔረሰብና ህዝቦች 873 ሺህ 272፣ ከኦሮሚያ ክልል 1.4 ሚሊዮን በላይ እና በአማራ ከ107 ሺህ በላይ ዜጎች የተፈናቀሉ እንደሆኑ ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚ/ር ከቡር አቶ ደመቀ መኮንን አገሪቱ ከድህነት ለመውጣት በአዲስ ለውጥ ጎዳና ላይ ባለችበት ወቅት እንዲህ ያለ አስነዋሪና አንገት የሚያስደፋ ተግባር መፈጸሙ የሚያሳዝን ሆኖ ሳለ የራሳቸውን ፍላጎት ለማሳካት ብለው በብሔር ውስጥ በመወሸቅ የንጹሀን ደም እንዲፈስ ባደረጉት አካላት ላይ የሚወሰደውን እርምጃ በማጠናከር ዜጎች በፈለጉበት ቦታ የመኖር፣ የመስራትና ሀብትን የማፍራት ህገ መንግስታዊ መብታቸውን የማስከበር ስራ በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚደራጅና በዚህ ተግባር የተሳተፉ አመራሮችም ሆኑ አንዳንድ የጸጥታ አካላት በራሳቸው ማፈር አለባቸውም ብለዋል፡፡   

የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል በወቅቱ ከም/ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡ ሲሆን በአንዳንድ አካባቢዎች ለተፈናቃዮች የተደረገውን ሰብዓዊ ድጋፍ በተመለከተ ተፈናቃዮችን ያላማከለ፣ በቂ ያለመሆንና በውቅቱ ተደራሽ ባለመሆኑ ሰፊ ክፍተት እንዳለ እንደምሳሌነትም በጌዴኦ ለተፈናቀሉት ዕርዳታው በወቅቱ ባለመድረሱ ለርሃብ መጋለጣቸውን በተመለከተ ለቀረበው ጥያቄ፤ ቀድመው ለተፈናቀሉት እርዳታው ተደራሽ ቢሆንም ቀጥሎ የተከሰተው ድንገተኛ በመሆኑ የተፈጠረ ክፍተት እንደሆነ ነው ምላሽ የሰጡት፡፡

በም/ቤቱ ከህግ የበላይነትን ከማረጋገጥ ጋር ተያይዞ ለአብነትም በደቡብ ክልል መስክ ምልከታው በተደረገባቸው በሁሉም አካባቢዎች ከተፈናቃዮች የተገኘው መረጃ መሰረት ለመፈናቀላቸው ዋናውን ሚና የተጫወቱት በየደረጃው ያሉት የአመራር አካላትና አንዳንድ የጸጥታ አካላት መሆኑን አንስተው አጥፊዎቹም በህግ ተጠያቂ አለመሆን በቀጣይም ወደ ቀያቸው ለመመለስም ከፍተኛ ስጋት ከመሆኑም ባሻገር በመንግስት በኩልም የህግ የበላይነት እየተከበረ አለመሆኑ አሳሳቢ እንደሆነ ተነስቶ በቀጣይ በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባ አሳስቧል፡፡

ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪያት በበኩላቸው የህግ የበላይነት የማረጋገጥ ስራ በቀጣይ ተጠናክሮ የሚቀጥልና ከተፈናቃዮች የተነሳው ተገቢ እንደሆነ አንስተው በአንዳንድ ክልል ለማፈናቀል ሚና የተጫወቱ ተጠርጣሪዎችን አውጥተው ያለመስጠትና ከለላ የማድረግ ሁኔታ በመኖሩ የዘገየ እንደሆነ አንስተው ለአብነት በቤንሻንጉል ከ183 ተጠርጣሪዎች 6ቱ ሲቀሩ ሌሎችን ወደ ህግ ፊት የማቅረብ ስራ ቢሰራም በሌላ በኩል በጉጂና ጌዴኦ አካባቢ ከሚፈለጉት ተጠርጣሪዎች 9 ብቻ መቅረባቸውን አብራርተዋል፡፡