«የኢትዮጵያ እና አልጀሪያ ፖለቲካዊ ትብብር እንደ ቀድሞው ተጠናክሮ ይቀጥላል» አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

(ዜና ፓርላማ) ሚያዝያ 13/ 2013 .. አዲስ አበባ፤ የኢትዮጵያ እና አልጀሪያ ፖለቲካዊ ትብብር እንደ ቀድሞው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ የተከበሩ ታገሰ ጫፎ ገለጹ፡፡

አፈ-ጉባኤው ይህንን የገለጹት የአልጀሪያን አምባሳደር ሚስተር ራቻድ ቢሎንስን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት ነው፡፡

ሁለቱ ሃገራት የቆየ የወዳጅነት ታሪክ እንዳላቸው ያወሱት አቶ ታገሰ፣ ግንኙነቱ በፖለቲካዊ ትብብር ሳይገድብ፣ በምጣኔ ሃብታዊ እና በማሕበራዊ ዘርፎችም ተጠናክሮ  እንደሚቀጥል ነው ያብራሩት፡፡

የምጣኔ ሃብት አድማሱን ለማስፋት እና የሁለቱ ሀገራት የንግዱ ማሕበረሰብ በጋራ የሚሰሩበትን መንገድ ለማመቻቸት ይረዳ ዘንድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአዲስ አበባ ወደ አልጀርስ በረራ እንዲኖረውም አፈ-ጉባኤው ከአምባሳደሩ ጋር ስምምነት ላይ  መድረሳቸውን ተናግረዋል፡፡

አፈ-ጉባኤ ታገሰ በፓን-አፍሪካ ፓርላማ ዙሪያ ከአምባሳደር ራቻድ ጋር የተወያዩ ሲሆን፣  ተቋሙ ተጠናክሮ የተሻለ አመራር እንዲኖረው ለማድረግ ሀገራቱ ከምርጫ በኋላ በጋራ እንደሚሰሩ አብራርተዋል፡፡

የአልጀሪያ አምባሳደር ራቻድ ቢሎንስ በበኩላቸው  የሁለቱን ሀገራት ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ትብብር ለማጠናከር ሀገራቸው እንደ ቀድሞው ሁሉ ከኢትዮጵያ ጋር ለመስራት ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል፡፡

አልጀሪያ የፊታችን ሰኔ 19 ብሔራዊ ምርጫ እንደምታካሂድ የተናገሩት አምባሳደሩ፣ ሀገራቸው ከምርጫው በኋላ የፓን-አፍሪካ ፓርላማን እና አመራሩን ለማጠናከር ከኢትጵያ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዛ እንደምትሰራ ነው የተናገሩት ፡፡

በስሜነው ሲፋረድ