(ዜና ፓርላማ)፤ ጥቅምት 1፣ 2015 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ስር የሰደዱ አንገብጋቢ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል መሆን እንዳለበት እና ሕዝቡም በየደረጃው ሊሳተፍበት እንደሚገባ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ገልጸዋል፡፡

ይህ የተገለጸው በዛሬው ዕለት የክልል ርዕሳነ-መስተዳድሮች እና ከፍተኛ አመራሮች ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ባቀረበው ስትራቴጂክ ዕቅድ እና አበይት የስራ ተግባራት ዙሪያ በተወያዩበት ወቅት ነው፡፡

ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ ውጤታማ ሆኖ ችግሮችን በየደረጃው ለመፍታት እንዲችል የሁሉም ኢትዮጵያውያን ንቁ ተሳትፎ ወሳኝ ሚና እንዳለው በውይይት መድረኩ ተነስቷል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ የተከበሩ ታገሠ ጫፎ፤ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ የሀገሪቱን ቁልፍ ችግሮች ለመፍታት ትልቅ ተስፋ የተጣለበት በመሆኑ በፍጥነት ወደ ሥራ መግባት እናዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ፣ የጋራ ማንነት ለመገንባት እና ቅቡልነት ያለው ሀገረ-መንግስት እንዲኖር ሀገራዊ ምክክሩ ወሳኝ ሚና እንዳለው የተከበሩ አቶ ታገሠ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ የኮሚሽኑን ስትራቴጂክ ዕቅድ እና በቀጣይ የሚያከናውናቸውን ተግባራት ባቀረቡበት ወቅት የሀገራዊ ምክክሩ ዋና ተዋናይ ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

አካታች ሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን የመንግስት ድጋፍ፣ ጠንካራ አመራርነት መስጠት፣ የውጭ ሀገራትን ጣልቃ-ገብነት መከላከል እና ሕዝባዊ ተሣትፎ እንዲኖር ማመቻቸት አይነተኛ የመፍትሄ አቅጣጫዎች መሆናቸውን ዋና ኮሚሽነሩ አስረድተዋል፡፡

የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ክቡር አቶ አደም ፋራህ፤ ሀገራዊ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን ገዥው ፓርቲ ብልጽግና አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸው፤ በምክክሩ ጥራትና ፍጥነት፣ አሳታፊነትና ውጤታማነት፣ እንዲሁም የኮሚሽኑና የሌሎች አካላት ሚና፣ በአካታችነትና በብቃት፣  በሀገር በቀልና በውጭ ሀገራት ድጋፍ ሰጭነት መካከል ሚዛናዊ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በሌላ በኩል ይህ ሀገር ለማሻገር ትልቅ ተስፋ የተጣለበት ሀገራዊ ምክክር እንዳይካሄድ እንቅፋት የሚፈጥሩ ሀይሎች ካሉ ለመከላከልና ለመቆጣጠር፣ አስፈላጊ ከሆነም መንግስት ተገቢውን እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ እንደሆነም የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንቱ  ክቡር አቶ አደም ፋራህ አስገንዝበዋል፡፡

የክልል ርዕሳነ-መስተዳድሮች፤ የዜጎችን አንኳር ችግርች በዘላቂነት ለመፍታት እምነት የተጣለበት ይህ ሀገራዊ ምክክር ስኬታማ እንዲሆን ሁለንተናዊ ድጋፍ ለማድረግ ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ የገጠሟትን የተወሳሰቡ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ሀገራዊ ምክክሩ አይነተኛ መሳሪያ እና አቅጣጫ ቀያሪ  እንደሆነ ያመኑበት የክልል ርዕሳነ-መስተዳድሮች፤ ሕዝቡ እንዲወያይባቸው በሚቀረጹ አጀንዳዎች ላይ በቂ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ የክልሎች አስተዋፅኦ ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ ሀገር ለማሻገር የሚያስችሉ ሀሳቦችን በማቅረብ ረገድ በቂ ተሳትፎ የሚያደርጉ እንደሆነም ከፍተኛ አመራሮቹ በውይይት መድረኩ አንስተዋል፡፡

ሀገራዊ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን ለሕዝቡ የሀሳብ ግልጸኝነት እና በቂ ግንዛቤ ለመፍጠር ሁለንተናዊ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ የገለጹት የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዮናስ አዳዬ፤ ሀገሪቱ አስተማማኝ ሰላም እንዲፈጠር በትብብር መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡  

ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት 
በፌስቡክ http://www.facebook.com/hoprparliament 
በዩቲዩብ https://www.youtube.com/watch?v=cp_8F5TEeFE
በቴሌግራም https://t.me/ParlamaNews 
በትዊተር http://twitter.com/fdrehopr 
በዌብሳይት www.hopr.gov.et ይከታተሉ