(ዜና ፓርላማ) ነሐሴ 17/2015 ዓ.ም፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ  አፈጻጸም  መርማሪ ቦርድ  የጀመረውን ክትትልና ቁጥጥር አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤ የተከበሩ ሎሚ በዶ  አስገነዘቡ፡፡

መርማሪ ቦርዱ እስካሁን ያከናወናቸውን ተግባራት ሪፖርት ካቀረበ በኋላ በቀጣይ የሚያከናውናቸውን ተግባራት በሚመለከት ያዘጋጀውን ረቂቅ ዕቅድ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ እና የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚንስትር በተገኙበት አቅርቧል፡፡

የምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባኤ የተከበሩ ወ/ሮ ሎሚ በዶ መርማሪ ቦርዱ የተለያዩ ተጽዕኖዎች ሳይበግሩት ገለልተኛ ሆኖ እያከናወነ ስላለው ተግባር ምስጋና አቅርበው፤ በቀጣይም የተፈጠረው አለመረጋጋት ተወግዶ የተሟላ ሰላም ይመጣ ዘንድ ክትትልና ቁጥጥሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል አስገንዝበዋል፡፡ 

በምክር ቤቱ የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚንስትር የተከበሩ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ እስካሁን ላከናወናቸው ተግባራት እውቅና ሰጥተው፤ በቀጣይም ገለልተኛ ሆኖ ስራውን ያከናውን ዘንድ ምክር ቤቱ አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

ዛሬ በነበረው የውይይት መድረክ መርማሪ ቦርዱ በቀጣይ የሚያከናውናችውን ተግባራት በሚመለከት ዝርዝር እቅድ እና የመተዳደሪያ ደንብ ቀርቦ የተለያዩ የማስተካከያ አስተያየቶች ቀርበውበት ጸድቋል፡፡  
(በአበባው ዮሴፍ)

ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት፡- 
በፌስቡክ http://www.facebook.com/hoprparliament 
በዩቲዩብ https://www.youtube.com/@FDREHOPR 
በቴሌግራም https://t.me/ParlamaNews 
በትዊተር http://twitter.com/fdrehopr 
በዌብሳይት www.hopr.gov.et ይከታተሉ።