(ዜና ፓርላማ)፤ ግንቦት 17፣ 2014፤ አዲስ አበባ፤ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ቀጣዩን በጀት ሀገራዊ ሁኔታዎችን አገናዝቦ እንዲበጅት አሳሰበ።

በዛሬው ዕለት በተካሄደው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ2015 ዓ.ም. በጀት-ተኮር ውይይት፤ ተቋሙ ነባራዊ ሀገራዊ ሁኔታዎችን ከግምት ያስገባ የበጀት ቀመር ሠርቶ እንዲያቀርብ ምክረ-ሐሳብ ተለግሶታል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ደሳለኝ ወዳጄ፤ በጀቱ ሀገራዊ ሁኔታን ያገናዘበ እና ወጪ ቆጣቢ መሆን እንዳለበት አመላክተዋል፡፡ ቋሚ ኮሚቴው ከመደበኛ እና የፕሮግራም በጀት ዝግጅት ጋር በተያያዘም፤ አስገዳጅ የሆኑትን ለመለየት ካለፈው ዓመት ጋር አስተያይቶ ውሳኔ እንደሚሰጥበት አስታውቀዋል፡፡

የሆነ ሆኖ ከዴሞክራሲ መገለጫዎች አንዱ ምርጫ በመሆኑ፤ በጀቱ፣ ገለልተኛነቱን ጠብቆ ጠንካራ እና ነጻ ሆኖ እንዲቀጥል የሚያስችል መሆን አለበትም ብለዋል፡፡ የቀረበውን በጀት ኮሚቴው በዝርዝር ካየው በኋላ መስተካከል ያለባቸው ካሉ አስተካክሎ፤ የበጀት ርዕሱን እና መጠኑን የያዘ ውሳኔ ቋሚ ኮሚቴው ለገንዘብ ሚኒስቴር እንደሚልክ አሳውቀዋል፡፡

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ እና ሌሎቹም የቦርዱ የሥራ ኃላፊዎች፤ ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫን ተከትሎ የሚደረገውን የአካባቢ ምርጫ ማከናወን፣ በተለያዩ ምክኒያቶች የስድስተኛው ዙር ምርጫ ባልተካሄደባቸው አካባቢዎች ምርጫ ማከናወን፤ የቀጣዩ በጀት ዓመት ተግባራት መሆናቸውን አስታውቀዋል። በባለፈው ምርጫ ወቅት ያጋጠሙ ችግሮችን መሠረት በማድረግ፤ ተቋማዊ የሰው ኃይልን መገንባት እና የመረጃ አያያዝን እና አጠቃቀምን ማዘመን፣ በ2015 የበጀት ዓመት ለማከናወን ካቀዷቸው ተግባራት ዋናዎቹ መሆናቸውን አያይዘው ጠቁመዋል፡፡

ከቀበሌ ምክር ቤቶች ውጪ፤ በሀገሪቱ ውስጥ የሚገኙትን ሰባ አምስት ዞኖች፣ ስምንት መቶ አርባ ሰባት ወረዳዎች፣ አንድ መቶ ሰባ ሁለት ከተማዎች፣ አሥራ አንድ ክፍለ-ከተማዎችን እና አንድ የብሔረሰብ ምክር ቤትን ያካተተ የአካባቢ ምርጫ ለማድረግ መታቀዱን ተናግረዋል፡፡ ምርጫው የሚከናወነው 56 ሺ 3 መቶ 73 የምርጫ ጣቢያዎችን በማደራጀት መሆኑን እና በዚህ ምርጫ ላይ 44 ነጥብ 4 ሚሊየን መራጭ ሊሳተፍ እንደሚችል ከወዲሁ ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡

በመሆኑም በቀጣዩ ዓመት ቦርዱ ሊሠራቸው ያሰባቸውን ሥራዎች ነጻ እና ገለልተኛ ሆኖ በጠንካራ የሰው ኃይል ለማከናወን፤ አጠቃላይ በጀት 6,940,713,563 (ስድስት ቢሊዮን ዘጠኝ መቶ አርባ ሚሊዮን ሰባት መቶ አሥራ ሦስት ሺህ አምስት መቶ ስድሳ ሦስት ብር) የሚያስፈልግ ሲሆን፣ ከዚህም ውስጥ 918,466,200 (ዘጠኝ መቶ አሥራ ስምንት ሚሊዮን አራት መቶ ስድሳ ስድስት ሺህ ሁለት መቶ ብር) ከአጋር ድርጅቶች ይገኛል ተብሎ እንደሚገመት አስረድተዋል፡፡

በመሆኑም፤ ከአጠቃላይ በጀቱ አምስት በመቶ መጠባበቂያን ጨምሮ፣ 6,022,247,363 (ስድስት ቢሊዮን ሃያ ሁለት ሚሊዮን ሁለት መቶ አርባ ሰባት ሺህ ሦስት መቶ ስድሳ ሦስት ብር) በመንግስት የሚሸፈን እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

በ ፋንታዬ ጌታቸው