(ዜና ፓርላማ)፤ ጥር 25፣ 2015 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 10ኛ መደበኛ ስብሰባው የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በገቢና ወጪ ምርት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት አመላክቷል፡፡

ምክር ቤቱ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን የ2015 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የዕቅድ አፈጻፀም ሪፖርት ገምግሟል፡፡

የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር አቶ ገብረመስቀል ጫላ የተቋማቸውን የዕቅድ አፈጻፀም ሪፖርት ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡

የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን የዕቅድ አፈጸፀም በተመለከተ ከቋሚ ኮሚቴው፣ ከሕዝብና ከምክር ቤት አባላት በርካታ ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን፤ ከቀረቡት ጥያቄዎች ውስጥም በወጪና ገቢ ምርቶች፣ በህገ-ወጥ ንግድ፣ በኑሮ ውድነት፣ በመሰረታዊ የምግብ ሸቀጦች፣ በነዳጅ፣ በሲሚንቶና በጫት ንግድ ዙሪያ ይገኙበታል፡፡

ለቀረቡት ጥያቄዎች ክቡር ሚኒስትሩ አቶ ገብረመስቀል ጫላና የስራ ባልደረቦቻቸው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ አሻ ያህያ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በርካታ ጠንካራ ተግባራትን ያከናወነ ቢሆንም አሁንም ያልተፈቱ በርካታ ችግሮች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

የገቢና የወጪ ምርት አፈጻጸም በቂ ባለመሆኑ በቀጣይም ህገ-ወጥ ንግድን በመከላከል በቁም እንስሳትና በጫት ላይ በትኩረት በመስራት ሀገሪቱ የሚገባትን ጥቅም ማስገኘት እንዳለበት እና በህገ-ወጥ ንግድ ላይ በተሰማሩ አካላት ላይም አስተማሪ የሆነ የቅጣት ዕርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

አያይዘውም ወደ ውጪ በሚላከው የጫት ምርት ላይ በየቦታው የሚታዩ ማነቆዎችን በመፍታት ሀገሪቱ፣ አምራቹና ነጋዴው ተገቢውን ጥቅም ማግኘት ይኖርበታል ሲሉም ነው ያስገነዘቡት፡፡

ዘይትን ጨምሮ የምግብ ፍጆታዎች አቅርቦት በቂ አለመሆኑን ጠቁመው፤ በቀጣይ አቅርቦቱን በማሻሻልና ስርጭቱን ፍትሀዊ በማድረግ በሕዝቡ ላይ እየደረሰ ያለውን የኑሮ ውድነት ጫና መቅረፍ እንደሚገባም ነው ያመላከቱት፡፡

በመጨረሻም አላሰራ የሚሉ ደንቦች፣ መመሪያዎችና አሰራሮች ካሉ ምክር ቤቱና ቋሚ ኮሚቴው ተገቢውን እገዛ እንደሚያደርጉም የተከበሩ ወ/ሮ አሻ ያህያ ተናግረዋል፡፡

ለቀረቡት ጥያቄዎች ክቡር ሚኒስትሩ አቶ ገብረመስቀል ጫላ እና ባልደረቦቻቸው በሰጡት ምላሽ የጠረፍ አካባቢዎችን ጨምሮ በሚደረግ ሕገ-ወጥ እና የኮንትሮባንድ ንግድ ሳቢያ ሀገሪቱ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንዳታገኝ ማድረጉን ጠቁመው፤ አሁን ላይ ተቋሙ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቁርጠኝነትና ተቀናጅቶ በመስራት ከፍተኛ ለውጥ ማምጣቱን ገልጸዋል፡፡

የኑሮ ውድነትን ለመቀነስም በርካታ የቅዳሜ ገበያዎችን በየቦታው በማቋቋም ለመፍታት መሞከሩን፣ የምግብ ፍጆታዎችን በተመለከተ አሁን ላይ በዘይት አቅርቦት ላይ ዕጥረት እንደሌለ፣ ነገር ግን በስኳር እና በስንዴ ዱቄት ላይ የታየውን ዕጥረት ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

በተመሳሳይም በሲሚንቶ ላይ የተከሰተው እጥረት ትክክለኛ መሆኑ ተገልጾ፤ መመሪያው የተሻሻለ እና በቅርቡም ማነቆው እንደሚፈታ እንዲሁም ነዳጅን በተመለከተ የናፍጣ እጥረት እንደሌለ የቤንዚን ዕጥረቱ የመጣው ለግዥ በተመደበው የውጭ ምንዛሬ ማነስ ሳቢያ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በቀጣይ እንደሀገር ችግሩን ሙሉ በሙሉ ለመቅረፍ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር እንዳይገቡ በማድረግ፣ የሕዝብ ትራንስፖርት እና የኤሌክትሪክ መኪናዎችን መጠቀም እንደሚገባም ነው የተጠቆመው፡፡

በ ኃይለሚካኤል አረጋኸኝ

ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

በፌስቡክ http://www.facebook.com/hoprparliament

በዩቲዩብ https://www.youtube.com/@FDREHOPR

በቴሌግራም https://t.me/ParlamaNews

በትዊተር http://twitter.com/fdrehopr

በዌብሳይት www.hopr.gov.et ይከታተሉ