(ዜና ፓርላማ)፣ ጥር 9፣ 2015፣ አዲስ አበባ፤ የኢፌደሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ8ኛ መደበኛ ስብሰባው፤ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እና ምክትል ፕሬዝዳንትን ሹመት መርምሮ አጸደቀ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ እንደገለጹት፤ የቀድሞው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እና ምክትል ፕሬዝዳንት ስልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቃቸውን አስታውሰው፤ በምትካቸው ዕጭዎቹን ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡ 

አፈ-ጉባኤው አያይዘውም፤ የፍትህ ተቋማት ነፃ እና ገለልተኛ ሆነው ሕዝቡ የሚያነሳቸውን የፍትህ ጣያቄዎች እንዲመለሱ ታስቦ ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ በእነዚህ ተቋማት መንግስት ሪፎርም ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

ከፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቶች ሹመት አስፈላጊነት ጋር በተያያዘ፤ ለምክር ቤት አባላት በገለጹበት ወቅት፤ የፍትህ ስርአቱን በበለጠ ለማጠናከር እና ፍትሃዊ የሆነ አግልግሎት ለመስጠት ታሳቦ መሆኑን አፈ-ጉባኤው አስረድተዋል፡፡

የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትሩ የተከበሩ አቶ ተስፋዬ በልጂጌ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እና ምክትል ፕሬዝዳንት እጭዎችን ለመሰየም ለምክር ቤቱ ባቀረቡበት ወቅት፤ የተሿሚዎቹን ግለ-ታሪክ በተለያዩ ቦታዎች ያገለገሉ እና የካበተ ልምድ ያላቸው በመሆኑ በፍትህ ተቋማት ላይ አስፈላጊውን እና የሚጠበቀውን ለውጥ ያመጣሉ ተብለው በመንግስት የታመነባቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው፤ በዕጩነት የቀረቡት ተሿሚዎች ካላቸው የስራ ልምድ አንጻር ቢሾሙ የፍትህ ተቋማትን በበለጠ በእውቀትና በክህሎት መምራት እንደሚችሉ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል፡፡

ከዚህ በፊት የፍትህ ስረዓቱ በርካታ ችግሮች ያሉበት መሆኑን የምክር ቤት አባላት ጠቁመው፤ በእጩነት የቀረቡት ተሿሚዎች የተሰጣቸውን ኃፊነት በታታሪነትና በአግባቡ መወጣት እንደሚችሉ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

በዚህም መሰረት ምክር ቤቱ፤ አቶ ቴዎድሮስ ምሕረት ከበደን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው እንዲሾሙ በእጩነት የቀረቡለትን በሶስት ድምጸ-ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ ውሳኔ ሃሳብ፤ ቁጥር 9/2015 አድርጎ አጽድቋል፡፡

በተመሳሳይም ምክር ቤቱ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንትነት በዕጩነት የቀረቡትን ወ/ሮ አበባ እምቢአለን ሹመት ውሳኔ ሃሳብ፤ ቁጥር 10/2015 አድርጎ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡

ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት 
በፌስቡክ http://www.facebook.com/hoprparliament 
በዩቲዩብ https://www.youtube.com/@FDREHOPR
በቴሌግራም https://t.me/ParlamaNews 
በትዊተር http://twitter.com/fdrehopr 
በዌብሳይት www.hopr.gov.et ይከታተሉ