(ዜና ፓርላማ)፣ ሰኔ 20፣ 2015 ዓ.ም፤ 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 2ኛ ዓመት የስራ ዘመን በ26ኛ መደበኛ ጉባዔው በ2014 በጀት ዓመት በፌደራል መንግሥት መስሪያ ቤቶች የፋይናንስ ሕጋዊነት ኦዲት እና የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ላይ ተወያይቷል፡፡

የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ዋና ኦዲተር መሰረት ዳምጤ በበጀት ዓመቱ በፌደራል መንግሥት መስሪያ ቤቶች የተከናወኑትን የፋይናንስ ሕጋዊነት ኦዲት እና የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት አቅርበው በምክር ቤቱ አባላት የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ቀርበዋል፡፡

በ2014 በጀት ዓመት የኦዲት ውጤት መሰረት ነቀፌታ የሌለበት 73፣ ከጥቂት ጉድለቶች በስተቀር አጥጋቢ ሆነው የተገኙ 66፣ አስተያየት መስጠት ያልተቻለባቸው 6 እና የጎላ ችግር ያለባቸው ሆኖ በመገኘታቸው ተቀባይነት የሚያሳጣ አስተያየት የተሰጠባቸው ደግሞ 19 ተቋማት ስለመሆናቸው በቀረበው ሪፖርት ተገልጿል፡፡

በበጀት ዓመቱ የተስተዋሉት የኦዲት ግኝቶች የጥሬ ገንዘብ እና የባንክ ሂሳብ አያያዝ፣ ውዝፍ ሂሳቦችን በወቅቱ አለመሰብሰብ እና አለማወራረድ፣ ተከፋይ ሂሳቦች፣ አለአግባብ የተከፈሉ ክፍያዎች፣ የገቢ ግብርና ታክስ አዋጅን አለመከተል፣ ደንብና መመሪያ ያልጠበቁ ግዢዎች፣ የውስጥ ገቢ አሰባሰብና አጠቃቀም፣ የበጀት አስተዳደር፣ በንብረት አጠቃቀም እና አስተዳደር የሚታዩ ጉድለቶች ዋና ዋናዎቹ ስለመሆናቸው ዋና ኦዲተር መሰረት ዳምጤ አስረድተዋል፡፡

በሌላ በኩል በበጀት ዓመቱ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በተደረጉ ክዋኔ ኦዲቶች በርካታ የአሰራር ስርዓቶች በየመስሪያ ቤቶቹ ተዘርግተው ባለመተግበራቸው ዋና ዋና ግድፈቶች ሆነው ስለመገኘታቸው በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

የታዩትን የአሰራር ጉድለቶችና ክፍተቶች ለማረምና ለማስተካከል የሚያስችሉ የመፍትሄ ሀሳቦችም በኦዲት ሪፖርቶቹ ስለመካተቱ ዋና ኦዲተሯ ገልጸዋል፡፡

አስተያየት ሊሰጥባቸው ያልቻለ የፋይናንስ እና ሕጋዊነት ኦዲት ሪፖርቶች እንዲሁም ተቀባይነት የሚያሳጣ አስተያየት የተሰጠባቸው ተቋማት ኦዲት ሪፖርት አንድ ላይ ተደራጅተው ለተከበሩ አፈ-ጉባዔ መላካቸውንና በሚመለከተው አካል ተመርምረው ተገቢ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባም ዋና ኦዲተሯ ተናግረዋል፡፡

በ አበባው ዮሴፍ

ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

በፌስቡክ http://www.facebook.com/hoprparliament

በዩቲዩብ https://www.youtube.com/@FDREHOPR

በቴሌግራም https://t.me/ParlamaNews

በትዊተር http://twitter.com/fdrehopr

በዌብሳይት www.hopr.gov.et ይከታተሉ