ምክር ቤቱ ከፈረንሳይና ከጣሊያን መንግሥታት ጋር የተደረጉ የመከላከያ ስምምነቶችጸደቀ

(ዜና ፓርላማ)፣ ሰኔ 22/2013 . የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 16 መደበኛ ስብሰባ ከፈረንሳይ እና ከጣሊያን መንግሥታት ጋር የተደረገውን የመከላከያ ትብብር ስምምነት ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ በሙሉ ድምጽ አጸደቀ።

የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስቴር ዴኤታ የተከበሩ አምባሳደር መስፍን ቸርትነት የትብብር ስምምነቶቹን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ አገራችን ኢትዮጵያ ወታደራዊ ልምድ ካላቸው አገራት ልምዶችንና ተሞክሮዎችን በመውሰድ ዘመኑ ከደረሰበት ወታደራዊ አቅም ደረጃ ለማድረስ፣ አንዱ የሌላውን ሉዓላዊነት በማክበር አገራት ሰላማዊ በሆነ መንገድ ግጭቶችን ለመፍታት ያላቸውን ቁርጠኝነት በመረዳት ከመከላከያ ዘርፉ ጋር በትብብር መስራት የሚያስችሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የምክር ቤት አባላትም ስምምነቱ የዘገየ መሆኑን ጠቁመው፤ ከቴክኒክ፣ ከልምድና ወታደራዊ አቅምን ከማሳደግ አንጻር  አስፈላጊ ቢሆንም፤ አንድ የውጭ አገር ወታደር በአንዲት ሉአላዊት አገር ወታደራዊ መለዮ ለብሶ መታየቱ፣ አገራዊ ሚስጢርን ከመጠበቅ አንፃር እና የወታደራዊ ስምምነቱ የቆይታ ጊዜን በተመለከተ ማብራሪያ እንድሰጣቸው ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ ወይዘሮ ብርቱካን አያኖ የወታደራዊ መለዩ ጋር በተያያዘ  የስልጠናና የመረጃ ልውውጥ እንጅ ወታደራዊ ግዳጅ ስላልሆነ መለዩ ችግር እንደሌለውና ወታደራዊ ሚሥጥርን ከመጠበቅ አንጻር በስምምነቱ ላይ በግልጽ እንደተቀመጠና የስምምነት የቆይታ ጊዜም ለአምስት ዓመት እንደሆና አንደ አስፈላጊነቱ ስምምነቱ እየታዳሰ ሊቀጥል እንደሚችል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ጌታቸው ኃይለማርያም በበኩላቸው፤ የአገሪቷን ወታደራዊ አቅም ለማጠናከር በውትድርናው ዓለም የካበተ ልምድ ካላቸው አገራት ሰፊ ውይይት ሲደረግ እንደቆየና ይህ ስምምነት በአገራችን ወታዳራዊ አቅም ግንባታ ጠቃሚታ እንዳለው አብራርተዋል፡፡

በመኩሪያ ፈንታ