ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 29ኛ መደበኛ ስብሰባ አራት ስምምነቶችን አፀደቀ
ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 29ኛ መደበኛ ስብሰባ አራት ስምምነቶችን አፀደቀ
---------------------
(ዜና ፓርላማ) ግንቦት 5 ቀን፣ 2017 ዓ.ም፤ 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን ባካሄደው 29ኛ መደበኛ ስብሰባው ሁለት የብድር ስምምነቶችን ፣ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን ማቋቋሚያ እና የአየር ትራንስፖርት ስምምነት አዋጆችን አፅድቋል።
የብድር ስምምነት ረቂቅ አዋጆቹን አስመልክቶ የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚንስትር ዴኤታ የተከበሩ ወ/ሮ መሰረት ሀይሌ ሞሽን ያቀረቡ ሲሆን አዋጆቹም በቀጥታ ወደ ሁለተኛ ንባብ ተሸጋግረውና ውይይት ተደርጎባቸው እንዲፀድቁም ጠይቀዋል።
ምክር ቤቱም ሞሽኑን በመደገፍ በአዋጆቹ ላይ በዝርዝር ተወያይቶ አፅድቋቸዋል።
የብድር ስምምነቶቹን አስመልክቶ የምክር ቤት አባላት በርካታ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን ያቀረቡ ሲሆን የገንዘብ ሚንስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በዚህም መሰረት በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እና በጣሊያን መንግስት መካከል ለአካባቢያዊና አረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት የበጀት ድጋፍ ማስፈጸሚያ የተደረገውን የብድር ስምምነት ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 1377/2017 ሆኖ በሙሉ ድምፅ ፀድቋል።
በተመሳሳይም በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እና በዓለም አቀፍ የልማት ማህበር መካከል ለመማር ማስተማር ማጎልበቻ የትምህርት ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ማስፈጸሚያ የተደረገውን የብድር ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 1378/2017 ሆኖ በሙሉ ድምፅ ፀድቋል።
በመቀጠልም በአፍሪካ ፋይናንስ ኮርፖሬሽን ማቋቋሚያ ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 1379/2017 ሆኖ በሶስት ድምፀ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል።
በመጨረሻም ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እና በኦስትሪያ ፌዴራል መንግስት መካከል የተፈረመውን የአየር ትራንስፖርት ስምምነት ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 1380/2017 ሆኖ በሙሉ ድምፅ በማፅደቅ ጉባኤውን አጠናቋል።
(በ ኃይለሚካኤል አረጋኸኝ)
Copyright 2020 - All rights reserved. House of Peoples' Representatives