ምክር ቤቱ የተለያዩ የብድር ስምምነቶችን መርምሮ አጸደቀ
(ዜና ፓርላማ) መጋቢት 8፣ 2016 ዓ.ም፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 17ኛ መደበኛ ስብሰባው የተለያዩ የብድር ስምምነቶችን መርምሮ አጽድቋል፡፡
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚንስትር የተከበሩ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ የብድር ስምምነቶቹ ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገት ጉልህ ጠቀሜታ እንዳላቸው ሰፊ ማብራሪያ ከሰጡ በኋላ ምክር ቤቱ መርምሮ እንዲያጸድቃቸው ጠይቀዋል፡፡
በዚህም መሰረት ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ እና በዓለም አቀፍ የልማት ማህበር መካከል የተደረገውን የዲጂታል መታወቂያ አካታችነትና አገልግሎት አሰጣጥ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል 228 ሚሊየን 200 ሺህ ኤስ.ዲ.አር የብድር ስምምነት ረቂቅ አዋጅ መርምሮ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡
ብድር ስምምነቱ ስድስት ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ38 አመታት ውስጥ የሚከፈል እንደሆነ የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትሩ የተከበሩ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ ገልጸዋል፡፡
በተመሳሳይም ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ እና በዓለም አቀፍ የልማት ማህበር መካከል ለትምህርትና ስልጠና ተግባራት ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል 200 ሚሊየን ዶላር የብድር ስምምነት በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡
ይህ ብድር የሀገሪቱን ልማትና ዕድገት ለማፋጠን ቁልፍ ሚና የሚጫወተውን የኢትዮጵያ ትምህርትና ስልጠና ለስራ ፈጠራ ፕሮጀክት ለማስፈጸም የሚረዳ እንደሆነ መንግስት ያመነበት መሆኑን የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡
ብደሩ የ6 ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ38 ዓመታት ውስጥ ተከፍሎ የሚያልቅ እንደሆነም ተብራርቷል፡፡
በኢትዮጵያ እና በዓለም አቀፍ የልማት ማህበር መካከል ለንግድ ሎጀስቲክስ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል የብድር ስምምነት በተመለከተ ምክር ቤቱ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ አጽድቋል፡፡ ለኢትዮጵያ ንግድ ሎጅስቲክስ የሚውል ብድር ገንዘብ 68 ሚሊየን 500 ሺህ ኤስ.ዲ.አር ነው፡፡
በብድር የተገኘው ገንዘብ የሞጆ ደረቅ ወደብን ሁለንተናዊ የሎጅስቲክስ አቅምና አፈጻጸም በማሳደግ አሁን ካለበት ደረጃ ለማሻሻል ከፍተኛ እገዛ የሚያደርግ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በተመሳሳይም ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ እና በጣልያን መንግስታት መካከል ለቦዬ ሐይቅ ዘላቂ ልማት ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል 83 ሚሊየን 500 ሺህ ዩሮ የብድር ስምምነት ረቂቅ አዋጅ መርምሮ አጽድቋል፡፡ ብድሩም የ16 ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ30 ዓመታት ውስጥ የሚከፈል እንደሆነ ማብራሪያ ተሰጥቶበታል፡፡
የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት የምታገኛቸው ገንዘቦች ለታለመላቸው ዓላማ ሊውሉ እንደሚገባ ገልጸው፤ እነዚህ የብድር ስምምነቶች የሀገሪቱን ሁለንተናዊ እድገት ለማፋጠን የሚግዙ መሆን እንዳለበቸው ተናግረዋል፡፡
የገንዘብ ሚንስቴር ሚንስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ(ዶ.ር) በበኩላቸው ከአለም አቀፍ ተቋማት የሚገኙ የገንዘብ ብድሮች በአግባቡ ስራ ላይ ውለው ሀገሪቱ የጀመረቻቸውን የልማት ፕሮጀክቶች ለማጠናቀቅ እና ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ትልቅ ፋይዳ እንዳላቸው አስገንዝበዋል፡፡
በሌላ በኩል ምክር ቤቱ በዛሬ ውሎው በኢትዮጵያ እና በጆርዳን መንግስታት መካከል በስራ ስምሪት ዘርፍ የተፈረመ የመግባቢያ ሰነድ ረቂቅ አዋጅ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡
Copyright 2020 - All rights reserved. House of Peoples' Representatives