ምክር ቤቱ የዜጎችን ግድያ ለማስቀረት የሚያግዝ ውሳኔ አስተላለፈ
(ዜና ፓርላማ)፤ ጥር 13፣ 2013 ዓ፣ም.፣ አዲስ አበባ፤ የኢፌዴሪ 5ኛው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት በ6ኛው ዘመኑ ባካሄደው 8ኛ መደበኛ ስብሰባ፤ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ በመተከል ዞን እና በሌሎች የሀገሪቱ አከባቢዎች የሚፈጸመውን የንፁሐን ግድያ፣ የአካል ጉዳት፣ መፈናቀል እና የንብረት መውደም ለማስቀረት የሚያግዝ የውሳኔ ሐሳብ መርምሮ አጸደቀ፡፡
በምክር ቤቱ የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) የውሳኔ ሐሳቡን ባቀረቡበት ወቅት፤ ግጭት በተፈጠረባቸው የተለያዩ አከባቢዎች የተጎዱ እና የተፈናቀሉ ዜጎችን ከመደገፍ እና ከማቋቋም አንፃር መንግስት እያደረገ ያለው እንቅስቀሴ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ችግሩን ከመሠረቱ የሚፈታ ሁሉን-አቀፍ የግንዛቤ ማስፋት እና የሕግ ማስከበር ሥራዎች መሠራት አለባቸው ብለዋል፡፡
የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከሕግ፣ ፍትሕ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጋር በመሆን በተሰጣቸው ኃላፊነት መሠረት ያዘጋጁት ይኼው ባለ አምስት ገጽ ሪፖርት እና የውሳኔ ሐሳብ፤ ሦስት ጭብጦችን እና ስድስት ዝርዝር የውሳኔ ሐሳቦችን የያዘ ነው፡፡ የምክር ቤቱ አባላትም በእነዚሁ ላይ ተመሥርተው ውይይት አካሂደዋል፡፡
በዚህም መሠረት በየደረጃው የሚገኙ አንዳንድ አመራሮች ሕዝብ እና መንግስት ለሰጣቸው ኃላፊነት ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ ከመሥራት ይልቅ ከጥፋት ኃይሎች ጋር በማበር፣ ችግሩ እንዲባባስ በማድረግ፣ በቀጥታም በተዘዋዋሪም እጃቸው እንዳለበት በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡ ችግሩንም ለማረም ከኮማንድ ፖስቱ ጋር የተጀመረው የሕግ ማስከበሩ ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እና አመራሩን በማጥራት በጥፋተኞች ላይ ተገቢው ሕጋዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ ርምጃ መወሰድ እንዳለበት የውሳኔ ሐሳቡ ያመላክታል፡፡
የውጭ የጥፋት ኃይሎች ከአንዳንድ ፅንፈኛ የሚዲያ አካላት ጋር በመቀናጀት የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ ለማደናቀፍ እና ድብቅ ዓላማቸውን ለማሳካት ሲጥሩ መቆየታቸውም በውሳኔ ሐሳቡ ተገልጿል፡፡ ስለሆነም መንግስት የውስጥ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ልማትን እና መልካም አስተዳደርን የማረጋገጥ ሥራ ከመሥራቱ በተጨማሪ፤ መገናኛ ብዙኃናት ሕግ እና ሥርዓትን ተከትለው እንዲሠሩ የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን ክትትል በማድረግ ሕግን በሚጥሱት ላይ ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ሥራ መሠራት እንዳለበትም ተያይዞ ተመላክቷል፡፡
ጥያቄ እና ሐሳባቸውን የሰነዘሩት የምክር ቤት አባላት ሁሉም የውሳኔ ሐሳቡ ተገቢ መሆኑን አምነው፤ ነገር ግን የዘገየ ከመሆኑም ባሻገር፣ አሁናዊ መፍትሔ ከመስጠት አኳያ ያለውን ክፍተት አመላክተዋል፡፡ መንግስት በተለይ በመተከል ዞን ተጠቂ የሕብረተሰብ ክፍሎችን አደራጅቶ እንዲያስታጥቅም ጠይቀዋል፡፡ ይሁን እንጂ የህብረተሰቡን ሰላም እና ደኅንነት ማስከበር የመንግስት ሥራ እና ግዴታ መሆኑ ከሪፖርት እና ውሳኔ ሐሳብ አቅራቢዎች ተገልጿል፡፡
መንግስት የሕብረተሰቡን የቆየ አብሮነት ለማስቀጠል ሕዝቡን ያሳተፈ ተከታታይ እና ቀጣይነት ያለው የፖለቲካ ሥራ መሥራት እንደሚገባው በውሳኔ ሐሳቡ ተጠቅሷል፡፡ በተጨማሪም ምክር ቤቱ በአትዮጵያ እና በኡጋንዳ ሪፐብሊክ መካከል የተደረገውን በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎችን አሳልፎ የመስጠት ስምምነትን፣ የኢትዮጵያ የካፒተል ገበያ ረቅቅ አዋጅን እንዲሁም የተለያዩ ሌሎች ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ አጽድቋል፡፡ የምክር ቤቱን የ6ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 7ኛ መደበኛ ስብሰባ ቃለ-ጉባኤም መርምሮ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡
ዘጋቢ ሚፍታህ ኪያር
Copyright 2020 - All rights reserved. House of Peoples' Representatives