ምክር ቤቱ የፌዴራል መንግስት በክልል ጣልቃ የሚገባበትን ስርዓት ለመደንገግ የወጣውን ማሻሻያ አዋጅ አጸደቀ
ምክር ቤቱ የፌዴራል መንግስት በክልል ጣልቃ የሚገባበትን ስርዓት ለመደንገግ የወጣውን ማሻሻያ አዋጅ አጸደቀ
-----------------------------
(ዜና ፓርላማ) መጋቢት 23 ፣ 2017 ዓ.ም፣ አዲስ አበባ፤ ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 22ኛ መደበኛ ስብሰባው የፌዴራል መንግሥት በክልል ጣልቃ የሚገባበትን ስርአት ለመደንገግ የወጣውን ማሻሻያ አዋጅ በሁለት ድምፅ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል።
የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) የማሻሻያ አዋጁ በአተገባበር ወቅት የታዩ ክፍተቶችን ከመሙላትም ባሻገር ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ክፍተቶችን ለመሙላት የሚያስችል እና ግልፅ አሰራር ለመዘርጋት ትልቅ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል፡፡
በተሻሻለው አዋጅ መሠረት የሚወሰደው እርምጃ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችልም ነው ብለዋል።
አክለውም የጊዜያዊ አስተዳደር ቆይታ ውሳኔ ላይ ጊዜያዊ አስተዳደሩ በትኩረት ሊሠራባቸው የሚገባቸው በውሳኔው ላይ ሊመላከት እንደሚገባ የተደነገገ መሆኑን ጠቁመው፣ ጊዚያዊ አስተዳደሩ ያስፈለገበት ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ እና ህገ መንግስታዊ ስርአቱን ለማፅናት እንደሆነም ገልፀዋል።
ምክር ቤቱም አዋጁን አስመልክቶ በስፋት ተወያይቷል፡፡
የፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሃና አርአያስላሴ በበኩላቸው ማሻሻያ አዋጁ ህገ - መንግስታዊ ስርዓቱን ለማስከበርም ሆነ የጊዚያዊ አስተዳደር የቆይታ ጊዜ ማራዘምን አስመልክቶ በምን ያህል ጊዜ እንደሚሻሻል ግልፅ አሰራር ለመዘርጋት እና ተጨማሪ ስራዎችን ለመስራት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
Copyright 2020 - All rights reserved. House of Peoples' Representatives