ምክር ቤቱ የፌዴራል ዋና ኦዲተር ያቀረበውን 2012 በጀት ዓመት የኦዲት ሪፖርት አዳመጠ

(ዜና ፓርላማ)፣ ሰኔ 22/2013 .ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 16 መደበኛ ስብሰባው የፌዴራል ዋና ኦዲተር ያቀረበውን የፌደራል ተቋማት 2012 በጀት ዓመት የሒሳብ ኦዲት ግኝት ሪፖርት አዳምጧል፡፡

ምክር ቤቱ የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ምክትል ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ ያቀረቡትን የኦዲት ሪፖርት ካደመጠ በኋላ የቀረበው ሪፖርት የሚበረታታ ቢሆንም በየዓመቱ ብዙ የገንዘብ ጉደለቶች እየታዩ ስለሆነ አስፈጻሚውን አካል አቅርቦ የመጠየቅና ለህግ የማቅረብ ጉዳይ የምክር ቤቱ ስልጣንና ተግባር በመሆኑ ለቀጣይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባ የተከበሩ አቶ ታደሰ መሰሉ ጠቁመዋል፡፡

የተከሩ አቶ ጴጥሮስ ወልደሰንበት በበኩላቸው የውስጥ ኦዲተሮችን አቅም በማጎልበትና ከአመራሩ ተፅዕኖ ነፃ እንዲሆኑ በማድረግ የተቋማትን የኦዲት ግኝት ክፍተቶች መቅረፍ እንደሚቻል አመላክተዋል፡፡

የተከበሩ አቶ ሻምበል ነጋሳ በየዓመቱ ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ሪፖርት ማቅረቡ በቂ ባለመሆኑ በተለይ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ እየታዩ ያሉትን የኦዲት ግኝቶች ለማረም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር አስተማሪ የሆነ ርምጃ መውሰድ እንደሚገባ ጠቁሟል፡፡

 

የዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ምክትል ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ የኦዲት ግኝቶችን ለማረም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ ቢሆንም ለውጥ እየመጣ ባለመሆኑ ለቀጣይ ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከጠቅላይ ዐቃባ ህግና ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩ አመላክተዋል፡፡

ወ/ሮ መሰረት አክለውም ምክር ቤቱ ተቋሙ አዲስ አደረጃጀት እንዲሰራ ድጋፍ እንዳደረገና ሁሉ ለቀጣይም የሰራተኞች የደመወዝ እስኬል በምክር ቤቱ ቢጸድቅላቸው ስራዎችን ይበልጥ ለመስራት አቅም እንደሚፈጥርላቸው ተናግረዋል፡፡

የምክር ቤቱ  ምክትል አፈ ጉባኤ የተከበሩ ወ/ሮ ሽታዬ ምናለ በበኩላቸው የተቋሙን የደሞዝ ስኬል ጥያቄ የአገሪቷን አቅም ባገናዘበ መልኩ ለመፍታት ምክር ቤቱ አስፈላጊውን ትብብርና እገዛ እንደሚያደርግ አመላክተዋል፡፡

በመኩሪያ ፈንታ