ምክር ቤቱ 38 ቢሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ በጀት አጸደቀ

(ዜና ፓርላማ ) ፣ ሰኔ 3 ቀን 2013 ዓ.ም.  ፤ አዲስ አበባ ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 14ኛ መደበኛ ስብሰባ ከሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበለትን ተጨማሪ በጀትና የወጭ አሸፋፈን ማስተካከያ ረቂቅ አዋጅ ወደ ሁለተኛ ንባብ አሸጋግሮ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል ፡፡

ምክር ቤቱ 38 ነጥብ 5  ቢሊዮን ብር የፌዴራል መንግስት ተጨማሪ በጀት እና የወጭ አሸፋፈን ረቂቅ አዋጅን  ያጸደቀ ሲሆን ፣ በጀቱ ከውጨ የሚገኘው የቀጥታ ድጋፍ በመቀነሱ ምክንያት፣ ለሚታዩ የኢኮኖሚ ተግዳሮቶች መፍትሄ ለመስጠት ፣ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ሕግን ለማስከበር ከተወሰደው እርምጃ ጋር ተያይዞ የተከሰቱ ወጪዎችን እንዲሁም ለጎርፍ መከላከል አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ የተከበሩ አቶ ጫኔ ሽመካ አስረድተዋል ፡፡

ተጨማሪ በጀቱ  በሃገር ውስጥ ባንክ ብድር የሚሸፈን ከሆነ የሀገር ውስጥ ባንኮች ገንዘቡን ከየት ያመጡታል? በጀቱ የዋጋ ግሽፈቱን እንደያባብሰው  በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል ምን ምን ስራዎች ተከናዉነዋል? በሕግ ማስከበሩ ጉዳት የደረሰባቸውን የአማራና አፋር ክልሎችን በምን መልኩ ለመደገፍ ታስቧል? የሚሉ ጥያቄ ከምክር ቤት አባላት ተነስተዋል ፡፡

የገንዘብ ሚኒሴር ሚኒስትር ዴኤታ  እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በበኩላቸው ተጨማሪ በጀቱ  የዋጋ ግሽፈቱን እንዳያባብሰው በጥንቃቄ እንደተሰራ ጠቁመው ፣ በጀቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተሰራው የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች መሰረት ኢኮኖሚው ካመነጨው ገንዘብ እንደሚሟላ አስረድተዋል፡፡

በሕግ ማስከበሩ ጉዳት የደረሰባቸውን ክልሎች በሴክተር ተቋማት እንደሚደገፉ ነው ሚኒስትር ዴኤታው ያብራሩት ፡፡

ምክር ቤቱም ረቂቅ አዋጁን አዋጅ ቁጥር 1247/2013 አድርጎ በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል ፡፡

በስሜነህ ሲፋረድ