(ዜና ፓርላማ)፤ ሐምሌ 21፣ 2014 ዓ.ም.፤ አዳማ፤ ሴቶች አብዛኛውን ጊዜያቸውን በማይከፈልባቸው የቤት ውስጥ ሥራዎች እንደሚያሳልፉ ተገለጸ፡፡

ይህ የተገለጸው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት ጋር በመተባበር ባዘጋጀው፤ የማይከፈልባቸውን የቤት ውስጥ ሥራዎች እና እንክብካቤዎች አስመልክቶ ለሴቶች ኮከስ አባላት በተሰጠው ስልጠና ላይ ነው፡፡

የኮከሱ ምክትል ሰብሳቢ ወይዘሮ ዓለሚቱ አበበ፤ ስልጠናው ሴቶች በአብዛኛው ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት በማይከፈልባቸው ሥራዎች መሆኑን እንዲገነዘቡ እንደረዳቸው ገልጸዋል። ይህንን ሁኔታ ለመለወጥም ሁሉም ከራሱ በመጀመር የሚጠበቅበትን ኃላፊነት መወጣት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

እነዚህን የሴቶች የስራ ጫናዎች ለመቀነስ በቀጣይ በምንሄድባቸው አካባቢዎች ሁሉ ትኩረት እንዲሰጣቸው ማድረግ አለብን ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ሁሉም ተቋማት የሴቶችን ጉዳይ በዕቅዳቸው ማካተት እንዳለባቸው እና ሕጎች እና ፖሊሲዎች ሲወጡም ራሳቸው ሴቶች አስተዋጽዖ ማበርከት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡

የሥራ ጫናን የሚቀንሱ ቴክኖሎጂዎችን ማስፋፋት፣ የተለያዩ መሠረተ-ልማቶች እንዲዳረሱ ማድረግ፣ ሴቶችን ማስተማር እና በሁሉም ዘርፍ ተሳታፊነታቸው እንዲጨምር የበለጠ መሠራት እንዳለበትም አመላክተዋል፡፡

የኮከሱ ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ አስቴር ከፍታው በበኩላቸው፤ ሴቶች በቤት ውስጥ የሚያከናውኗቸው የማይከፈልባቸው የቤት ውስጥ ሥራዎች እና እንክብካቤዎች ዋጋ ቢሰጣቸው ለኢኮኖሚው ከፍተኛ አስተዋጽዖ የሚያበረክቱ መሆናቸውን በመረዳት፣ ሁሉም ባለድርሻ አካል የራሱን ኃላፊነት በመወጣት፤ የሴቶችን የሥራ ጫናም ለመቀነስ መጣር አለበት ብለዋል፡፡

ሥራን ተከፋፍሎ በመሥራት ረገድ ያለውን የተዛባ አመለካከት ለመቀየርም፤ ሴቶችን ብቻ ሳይሆን ወንዶችንም ማሰልጠን አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ስልጠናውን የሰጡት በሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሴቶች ማካተት እና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ዳይሬክቶሬት የተቋማት ዓቅም ማጎልበት ባለሙያ አቶ እንየው ታምሩ፤ ሴቶች የሚያከናውኗቸው የማይከፈልባቸው ሥራዎች ለዓለም-አቀፉ ኢኮኖሚ 13 በመቶ አስተዋጽዖ እንዳላቸው ገልጸዋል።

78 በመቶ የሚሆኑት ወንዶች ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት በሚከፈልባቸው ሥራዎች ሲሆን፤ 93 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ደግሞ በማይከፈልባቸው ሥራዎች ላይ መሆኑን ስልጠናውን በሰጡበት ወቅት አያይዘው አብራርተዋል፡፡

በ ፋንታዬ ጌታቸው