ቋሚ ኮሚቴው ኤጀንሲው ያልሰበሰበው 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ውዝፍ የጡረታ መዋጮ መኖሩን አረጋገጠ

(ዜና ፓርላማ )፣ ግንቦት 25 ቀን 2013 ዓ.ም.፣ አዲስ አበባ፤ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የመንግስት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከመንግስት ሠራተኞች ያልሰበሰበው 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ውዝፍ የጡረታ መዋጮ መኖሩን አረጋግጧል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ይህን ያረጋገጠው ሰሞኑን የኤጀንሲውን የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት በገመገመበት ወቅት ነው፡፡

ኤጀንሲው ከመንግስት ሠራተኞች ጡረታ ገንዘብ አሰባሰብ ጋር ተያይዞ በፌዴራልና ክልል ሚገኙ የመንግሥት ሥሪያ ቤቶች በወቅቱና በተገቢው መጠን ገቢ አለማድረጉን ከቀረበው ሪፖርት የተረዱት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ እምየ ቢተው ተቋሙ ችግሩን ለመፍታት በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡

ባለፉት 5 ዓመታት ብቻ ገቢ ያልሆነ 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር እንዲሁም 2013 ዓ.ም. ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ 1 ነጥብ 21 ቢሊየን ብር በኦዲት መገኘቱን ያብራሩት ወ/ሮ እምየ 1 ነጥብ 21 ቢሊዮን ብሩ ውስጥ 107.06 ሚሊየን ብር ብቻ ገቢ መደረጉን መረዳታቸውን ነው የተናገሩት፡፡  

ኤጀንሲው እነዚህንና ሌሎች እየተንከባለሉ የመጡ ውስብስብ ችግሮችን ለመፍታት የመንግስት ሰራተኞች የጡረታ አዋጅንና የኤጀንሲውን ማቋቋሚያ ደንብ ለማሻሻል የቀረቡ ሁለት ረቂቅ ሰነዶችን ተከታትሎ ማጸደቅ እንዳለበትም ወ/ሮ እምዬ ጠቁመዋል፡፡

ኤጀንሲው ያለበትን የሰው ኃይል እጥረት በመፍታትና አዳዲስ ለሚቀጠሩ ሠራተኞች የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናዎችን በመስጠት ያከናወናቸውን ተግባራት እና አሰራሩን   ለማዘመን ያደረገውን ጥረት ወ/ሮ እምዬ በጥንካሬ አንስተዋል፡፡

በሌላ በኩል ከጡረተኞች ክፍያ መዘግየት ጋር ተያይዞ ጡረተኞች ለሚያነሱት ቅሬታ  አፋጣኝ ምላሽ አለመስጠቱን፣ በገቢ አሰባሰብ ረገድ የአሰራር ጥሰት በፈጸሙ ተቋማት ላይ ተጠያቂነት አለማረጋገጡን፣ ከውዝፍ ገቢ ጋር ያሉ ችግሮችን ለቅረፍ ከክልሎችና ከፈዴራል መስሪያ ቤቶች ጋር ተቀናጅቶ አለመስራቱን በውስንነት ያነሱት ሰብሳቢዋ፤ ኤጀንሲው ውስንነቶቹን  በቀሪ ወራት በማካካስ ተግባራዊ እንዲያደርግ አሳስበዋል፡፡

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳባ ኦሪያ በበኩላቸው በቋሚ ኮሚቴው የተጠቀሱት ችግሮች መኖራቸውን አምነው፤ ችግሮቹን ለመፍታት ከፌዴራል እስከ ክልል ድረስ አሰራሮችን በመዘርጋት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል ፡፡

ኤጀንሲው 187 ሺህ ለሚጠጉ የጡረታ ተገልጋዮች ክፍያ በባንክ በኩል እንዲስተናገድ መደረጉን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

በደርብ ሙሉዬ