ቋሚ ኮሚቴው የዴሞክራሲ ተቋማትን በበጀት ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አስገነዘበ

(ዜና ፓርላማ)፣ ግንቦት 17 ቀን 2013ዓ/ም፤ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢ፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የ2014 ዓ/ም የበጀት ጥያቄን አስመልክቶ ከዴሞክራሲ ተቋማት ጋር ውይይት ባደረገበት ወቅት፣ በአገሪቱ የሚከሰቱ ቀውሶችን ለመግታት ተቋማቱን በበጀት ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አሳስቧል፡፡

ለ2014 ዓ/ም ለገንዘብ ሚኒስቴር የበጀት ጥያቄ ያቀረቡ የዴሞክራሲ ተቋማት አራት ሲሆኑ በቀጣይ በጀት አመት ውስጣዊ አደረጃጀታቸውን በማሻሻል ውጤታማ ስራዎችን ለማከናወን እንዳቀዱ ነው ቋሚ ኮሚቴው የተገነዘበው፡፡

በዚህም መሰረት የኢትየጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ለ2014 ዓ/ም የጠየቀው በጀት 211.6 ሚሊየን ብር ሲሆን፣ በገንዘብ ሚኒስቴር የተፈቀደለት የበጀት ጣሪያ 103 ሚሊየን ብር፣ የፌዴራል የስነ-ምግባር እና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ደግሞ 300 ሚሊየን 815 ሺህ ብር እንዲፈቀድለት ጠይቆ 109 ሚሊየን 587 ሺህ ብር የተፈቀደለት መሆኑን ቋሚ ኮሚቴው መታዘብ ችሏል፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽ/ቤትም ለ2014 ዓ/ም መደበኛ በጀት 442 ሚሊየን 194 ሺህ ብር የጠየቀ ሲሆን 337 ሚሊየን 863 ሺህ ብር ተፈቅዶለታል፡፡ የካፒታል በጀትን አስመልክቶ ጽ/ቤቱ 174 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር እንዲመደብለት ጥያቄ አቅርቦ የተፈቀደለት የገንዘብ ጣሪያ 59 ሚሊዮን ብር እንደሆነ ነው ቋሚ ኮሚቴው መረዳት የቻለው፡፡

በተመሳሳይም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና የኢ.ፌ.ዴ.ሪ እንባ ጠባቂ ተቋም የ2014 ዓ/ም የበጀት ፍላጎታቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ 192 ሚሊየን 800 ሺህ ብር ጠይቆ የተፈቀደለት 92 ሚሊየን 551 ሺህ ብር መደበኛ በጀት ጣሪያ ሲሆን፣ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ እንባ ጠባቂ ተቋም ደግሞ 85 ሚሊየን የበጀት ጣሪያ የተላለፈለት ሲሆን የተቋሙ የ2014 ዓ/ም በጀት 16 በመቶ ጭማሪ እንደታየበት ነው በውይይቱ የተገለጸው፡፡

በገንዘብ ሚኒስቴር የበጀት ጉዳዮች አማካሪ አቶ ተፈሪ ደመቀ እንደገለጹት የ2014 ዓ.ም በጀት እንዲፀድቅላቸው ከጠየቁት የዴሞክራሲ ተቋማት መካከል የኢ.ፌ.ዴ.ሪ እንባ ጠባቂ ተቋም በአንጻራዊነት የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበና በበጀት አመቱ ለመስራት ባሰበው ልክ በጀት የጠየቀ መሆኑን ገልጸው የቀሩት ተቋማት የተጋነነ የበጀት ጥያቄ ያቀረቡ በመሆኑ እንደገና ማየት እንዳለባቸው እና ተቋማቱ ከተመደበላቸው በጀት በላይ የሚጠይቁና የማይታለፉ ስራዎች ካሉ በቂ ሰነድና ማብራሪያ ማቅረብ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

አቶ ተፈሪ አያይዘውም ተቋማት የሀገሪቱን የኢኮኖሚ አቅም ከግንዛቤ በማስገባት ስራቸውን በብቃት እና በጀት ቆጣቢ በሆነ መንገድ ማከናወን አለባቸው ሲሉም አክለዋል፡፡

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢ፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ ያየሽ ተስፋሁነኝ በበኩላቸው የዴሞክራሲ ተቋማት በአገሪቱ የሚከሰቱ ቀውሶችን ለማርገብ ትልቅ ፋይዳ ያላቸው በመሆኑ በበጀትም ሆነ በሰው ሀይል ማጠናከር እንደሚገባ ጠቁመው፤ በጀቱ በቀጣይ  የሚታይ መሆኑን ነው ያመላከቱት፡፡

በተስፋሁን ዋልተንጉስ