(ዜና ፓርላማ)፤ ጥር 14 ቀን 2013 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰሞኑን በጂማ ዩኒቨርስቲ ባዳረገው የመስክ ምልከታ ዩኒቨርሲቲው በፌደራል ዋና ኦዲተር የተሰጠውን የሂሳብ ኦዲት ግኝት አስተያየት ፈጥኖ ማረም እንዳለበት አሳሰበ፡፡

የቋሚ ኮሚቴው የፋይናንስ ዘርፍ ንዑስ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ ሶፊያ አልማሙን እንደገለጹት፤ ዩኒቨርስቲው በፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የተሰጠውን የኦዲት ግኝት አስተያየት እንደ ግብዓት በመውሰድ ለቀጣይ በትኩረት መስራት እንዳለበት ጠቁመው፤ ለስፔሻለይዝድ ሆስፒታሉ የእንግዳ ማረፊያ እና ለመድሀኒት ግዢ የወጣው ወጪ ላይ ተገቢውን የፋይናንስ ህግ ሳይከተሉ የተከፈሉ ክፍያዎች የህዝብ ሀብት መሆናቸውን በመገንዘብ ዩኒቨርሲቲው የሂሳብ አየያዝ አሰራሩን ማሻሻል እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው፤ ዩኒቨርስቲው የተሰብሳቢ ሂሰብ ኦዲት ሲደረግ በበጀት አመቱ መጨረሻ በተሰብሳቢ ሒሳብ ውስጥ በግዜ ገደብ ያልተወራረደ እና ከአንድ ወር እስከ አምስት ዓመት በተሰብሳቢነት የቆየ 32 ሚሊዮን ብር መኖሩ በኦዲት ግኝቱ ስለተረጋገጠ ዩኒቨርሲቲው ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርቦ በመስረት የኦዲት ግኝቱን በፍጥነት ማረም ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በበኩላቸው የዩኒቨርስቲው አመራር አካላት የፋይናንስ ስርዓትን ተከትሎ አለመስራት የህግ ተጠያቂነትን እንደሚያስከትል  በመረዳት ዩኒቨርሲቲው አሁን ካለበት የኦዲት አፈጻጸም ጉድለት ወጥቶ ወደ ትክክለኛ የሂሳብ አሰራር  መግባት እንዳለበት በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡

የዩኒርስቲው ፕሬዝዳንት ጀማል አባፊጣ (ዶ/ር) በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲው በርካታ የኦዲት ግኝቶች ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮች መሆናቸውን ጠቁመው የታዩት የኦዲት ግኝቶች አብዛኛዎቹ እየተቀረፉ መምጠተቸውን እና በቀጣይም ችግሩን ሙሉ በሙሉ ለመቀረፍ ጠንክረው እንደሚሰሩ  ገልጸዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ሚፍታህ ኪያር