(ዜና ፓርላማ)፤ ሰኔ 21፣ 2014 ዓ.ም.፤ አዲስ አበባ፤ በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባዔ ወይዘሮ ሎሚ በዶ የተመራው ባለአምስት አባላት ልዑክ፤ በፓን-አፍሪካ ፓርላማ ጉባዔ እየተሳተፈ ይገኛል፡፡

በትናንትናው ዕለት በተጀመረው በዚህ ጉባዔ፤ የአፍሪካ ሕብረት ሰብሳቢ አቶ ሙሣ ፋቂ ማሃማት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፤ አዳዲስ የአህጉራዊው ምክር ቤት አባላትም ቃለ-መሃላ ፈጽመዋል፡፡

የፓን-አፍሪካ አመራሮች ፕሬዚዳንት እና ምክትል ፕሬዚዳንቶች እንዲሁም የተለያዩ ኮሚቴዎች ምርጫ ለማካሄድ በሚቻልበት ሁኔታ ለጉባዔው ቀርቦ እንዲወሰን፤ ክርክር እየተደረገ ይገኛል።

ምርጫው ለ5ቱም የአፍሪካ ቀጠናዎች ፍትሐዊ ውክልና እንዲኖር ያስችል ዘንድ ለአፍሪካ ሕብረት ፓርላማ የወቅቱ ኃላፊዎች ሐሳብ እና የምርጫ ማስፈጸሚያ አማራጭ መንገዶች ቀርበዋል።

ይኼው ለ6 ቀናት የሚቆየው የሕብረቱ ፓርላማ ጉባዔ፤ በተቀመጡት አቅጣጫዎች መሠረት በበርካታ አህጉራዊ ጉዳዮች እንደሚነጋገር ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመላክታል፡፡