በአገሪቱ በአንዳንድ አካባቢዎች በተከሰቱ ችግሮች ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ ለችግሮቹ መፍትሄ መፈለግ ላይ ሊተኮር እንደሚገባ ክቡር አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ አሳሰቡ

(ዜና ፓርላማ) ሚያዚያ 17 ቀን 2013 ዓ.ም.፣ አዲስ አበባ፤ የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈ-ጉባኤ የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ በአገሪቱ በአንዳንድ አካባቢዎች በተከሰቱ ችግሮች ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ ለችግሮቹ መፍትሄ መፈለግ ላይ ሊተኮር እንደሚገባ  የገለፁት ሰሞኑን በምርጫ ክልላቸው በመገኘት የምርጫ ካርድ በወሰዱበት ወቅት ነው፡፡

በሁሉም አካባቢ የሚኖሩ ብሄር ብሄረሰቦች ለዘመናት ተከባብረው የኖሩ፣ በደም የተሳሰሩ የውጪ ጠላትንም ጭምር በጋራ የመከቱና ለሀገር የወደቁ ከፍተኛ ስነ-ልቡና ያላቸው ኩሩ ህዝብ ናቸው ብለዋል፡፡

ሰሞኑን በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች በጊዜ ሂደት የሚፈቱ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም የህዝቡን አንድነትና ህብረት ማጠናከር፣ የተዛቡ ትርክቶችን ማስተካከል እና እጅ ለእጅ በመያያዝ የሀገሪቱን ብልጽግና ማረጋገጥ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት፡፡

በሀገሪቱ ከምርጫ ውጪ ወደ ስልጣን የሚመጣበት መንገድ ባለመኖሩ መንግስትም ሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በሰላማዊ መንገድ ማኒፌስቷቸውን ለህዝቡ በማስተዋወቅ ምርጫውን ማካሄድ እና በመምርጫው የሚገኘውንም ውጤት በፀጋ ለመቀበል ዝግጁ መሆን እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

ከፊታችን በሚካሄደው ምርጫም ዜጎች የምርጫ ካርድ በመውሰድ ይበጀኛል የሚሉትን ፓርቲ መምረጥና ብልጽግናም ሆነ ሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች የህዝብን ድምጽ ማክበር እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡

የተከበሩ አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ የብልጽግናን ፓርቲ በመወከል ለፌደራል የህዝብ ተወዮካዮች ምክር ቤት በእጩነት መቅረባቸው ታውቋል፡፡

በኃ/ሚካኤል አረጋኽኝ