(ዜና ፓርላማ)፣ ህዳር 6፣ 2015 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ በጦርነቱ የተጎዱ ዜጎችን የመደገፍና የማቋቋም ስራ በትኩረት እንደሚሰራ ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ገልፀዋል።

ክቡር ጠቅላይ ሚንስትሩ ይህን ያሉት ከምክር ቤት አባላት የቀረቡላቸውን ጥያቄዎች መነሻ በማድረግ በሰጡት ማብራሪያ ነው።

በጦርነቱ ለተጎዱ ዜጎች ምግብን ጨምሮ ልዩ ልዩ እርዳታዎች በማቅረብ የመደገፍ፣ የተጎዱ መሰረተ ልማቶችን መልሶ የመገንባት ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን እና በቀጣይም በግጭቱ ሳቢያ የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ የማስፈር ተግባራት እንደሚከናወኑም ነው ጠቅላይ ሚንስትሩ  የተናገሩት፡፡

የፍትህ ስርዓቱን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፤ የፍትህ ስርዓቱ ስብራት እንደገጠመው፣ በፍትህ ስርዓቱ ውስጥ በሀቅ የሚሰሩ አካላት እንዳሉ ሁሉ ያለጉቦ የማይሰሩ መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡

ይህን ችግር ለማስተካከል የሁሉንም አካል ርብርብ እንደሚጠይቅ እና የፓርላማ ድርሻ ግን የጎላ መሆኑን ነው ያመላከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሌብነትና የመልካም አስተዳደር ችግር በአመራሩ እና በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥም እንደሚታይ አብራርተዋል፡፡

ለዚህ ችግር አሁናዊ መፍትሄ ካልተበጀለት የሀገርን ኢኮኖሚ በእጅጉ ሊጎዳ እንደሚችል አሳስበው፤ በመንግስት በኩልም በቀጣይ ጠንካራ የማስተካከያ ስራዎች እንደሚሰሩም ነው ያመላከቱት፡፡

ዲፕሎማሲን በተመለከተ የአፍሪካውያንን ችግር በፍሪካውያን በሚል መርህ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ስራዎች መሰራታቸውን ገልፀው፤ በተለይ ባለፉት 3 ወራት የጎረቤት ሀገራት ከሆኑት ከኤርትራ፣ ከሶማሊያና ከሱዳን ጋር ጥሩ ግንኙነት መፈጠሩን እንዲሁም ከአሜሪካ እና ከአውሮፓ ሀገራት ጋርም ተመሳሳይ ስራ መሰራቱን እና ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ያብራሩት፡፡

በሀገሪቱ ለተፈረመው የሰላም ስምምነት የእነዚህ አካላት ድጋፍ እና ሚና ከፍተኛ ስለነበር ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡  

በ ኃ/ሚካኤል አረጋኸኝ

ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት 
በፌስቡክ http://www.facebook.com/hoprparliament 
በዩቲዩብ https://www.youtube.com/channel/UCZm9CZOqIyp8qesP3XkVBPg
በቴሌግራም https://t.me/ParlamaNews 
በትዊተር http://twitter.com/fdrehopr 
በዌብሳይት www.hopr.gov.et ይከታተሉ