(ዜና ፓርላማ)፤ ሰኔ 6፣ 2014 ዓ.ም.፤ አዲስ አበባ፤ ብሔራዊ የመረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ያካሄደውን የለውጥ (Reform) ሥራ ተከትሎ የተቋሙን ማቋቋሚያ አዋጅ ማሻሻል አስፈላጊ መሆኑን፤ በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች እንዲሁም የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች፤ ከአስረጂዎች ጋር ባካሄዱት የጋራ የምክክር መድረክ ተገለጸ፡፡

ይህ የተገለጸው፤ ቋሚ ኮሚቴዎቹ ብሔራዊ የመረጃ እና ደኅንነት አገልግሎትን እንደገና ለማቋቋም የወጣውን አዋጅ ቁጥር 804/2005 ለማሻሻል በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ከብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በዛሬው ዕለት በተወያዩበት ወቅት ነው፡፡

የሕግ፣ ፍትሕ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወይዘሮ እፀገነት መንግስቱ፤ የተቋሙ ዋነኛ ሥራ የሀገርን ደኅንነት መጠበቅ እና ጥቅምን ማስከበር በመሆኑ፤ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ለመወጣት እንዲችል አዋጁ ተሻሻሎ መቅረቡን ገልጸዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴዎቹ አባላት በበኩላቸው፤ ተቋሙ ከዚህ በፊት ደርግን ጨምሮ በነበሩ የመንግስት ሥርዓቶች የዜጎች ማፈኛ እና ማሰቃያ እንደነበር አስታውሰው፤ ከለውጡ ወዲህ ግን በርካታ የሪፎርም ሥራዎች በመሠራታቸው፣ ተቋሙ ወደ ዜጎች ደኅንነት ጠባቂነት እንዲሁም ጋሻ እና መከታነት መሸጋገሩን አብራርተዋል፡፡

አያይዘውም፤ ተቋሙ ራሱን በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች በማዘመን ላይ መሆኑን በምልከታቸው ማረጋገጣቸውንም ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በፊት የነበረው አዋጅ ይህንን በሚመጥን መልኩ ስላልተቀረጸ፤ ለመሻሻል መቅረቡ ተገቢነት እንዳለውም ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ በረቂቅ አዋጁ በአዲስነት በተካተቱ እና በተሻሻሉ አንቀጾች ላይ ማብራሪያ በሚሹ እና ግልጽነት ይጎድሏቸዋል ያሏቸውን ጉዳዮች፤ በጥያቄ እና በአስተያየት መልክ አቅርበዋል፡፡

የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት ዳይሬክተር ጄኔራል ተመስገን ጥሩነህ፤ በአዋጁ አስፈላጊነት ዙሪያ እንዲሁም በኮሚቴው አባላት ለቀረቡ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ማብራሪያ እና ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ከለውጡ ወዲህ፤ ተቋሙ፣ የሀገርን ደንንነት ለማስጠበቅ፣ በሕዝብ ዘንድ ዕምነት እንዲጣልበት፣ በጠላት ደግሞ እንዲፈራ ለማድረግ በርካታ የዘርፉን ሥራዎች በማከናወን ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ሥራውን የሚያከናውነው ዋነኛው መሣሪያ የሰው ኃይል በመሆኑ፤ በዘርፉ የሚሰማሩ ባለሙያዎች ከማንኛውም ፖለቲካ ገለልተኛ የሆኑ እና በየትኛውም የመንግስት ለውጥ የማይናወጥ ተቋምን የሚፈጥሩ መሆን እንዳለባቸው ዳይሬክተር ጄኔራሉ አስረድተዋል፡፡ ለዚህም ሲባል የሰው ኃይል አደረጃጀት፣ የደመወዝ እና ጥቅማ-ጥቅም፣ ከግዢ ሥርዓት ጋር የተያያዙ እንዲሁም የሥነ-ልቦና ጦርነትን ለመከላከል የሚያስችሉ ጉዳዮች በዋናነት በተሻሻለው ረቂቅ አዋጅ ውስጥ መካተታቸውን አብራርተዋል፡፡

ምክር ቤቱ ግንቦት 11 ቀን 2014 ዓ.ም. ባካሄደው 8ኛ መደበኛ ስብሰባው፤ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎትን እንደገና ለማቋቋም የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 7/2014 ሆኖ በዋናነት ለሕግ፣ ፍትሕ እና ዴሞክራሲ እንዲሁም በተባባሪነት ለውጭ ግንኙነት እና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች ለዝርዝር ዕይታ የመራ መሆኑ ይታወሳል፡፡ በቀጣይም ቋሚ ኮሚቴዎቹ ከባለድርሻ አካላት ጋር ይፋዊ ውይይት ካደረጉ በኋላ፤ ለምክር ቤቱ ቀርቦ ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በ ኃይለሚካኤል አረጋኸኝ