(ዜና ፓርላማ)፣ ታህሳስ 14፣ 2015 ዓ.ም.፤ በኢትዮጵያ የኖርዌይ አምባሳደር እና በአፍሪካ ሕብረት የኖርዌይ ቋሚ ተወካይ አምባሳደር ስቲያን ክሪስቲንሰን ሀገራቸው ኖርዌይ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን የሰብዓዊ እርዳታ ድጋፍና የመልሶ መቋቋም ሂደት አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታውቀዋል።

አምባሳደሩ ከኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግኑኝነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ዲማ ኖጎ (ዶ/ር) ጋር በተወያዩበት ወቅት ኖርዌይ በኢትዮጵያ የሰሜኑ ክፍልና በሌሎች አካባቢዎች በተፈጠረው ግጭት ምክንያት የተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎችን እና መሰረተ-ልማቶችን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጸዋል።

መንግስት ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እያደረገ ያለውን ጥረት የኖርዌይ መንግስት እንደሚያበረታታ የገለፁት አምባሳደር ስቲያን ክሪስቲንሰን፤ በግጭቱ ወቅት እንዲቆሙ የተደረጉ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን እንደገና ወደ ስራ ለማስገባት እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውንም ጠቁመዋል።

በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግኑኝነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ነጎ (ዶ/ር) በውይይቱ ወቅት እንደገለፁት፤ ሀገራችን ካጋጠማት ችግር ወጥታ የዜጎችን ሁለንተናዊ እድገት የሚያረጋግጡ ስራዎች ለማስቀጠል ሰላም ወሳኙን ሚና ይጫወታል ያሉ ሲሆን በግጭቱም ወቅት የተጎዱ ዜጎችን መልሶ በማቋቋም እና በግጭቱ የወደሙ መሰረተ-ልማቶችን በመገንባት ሂደት የአጋር ሀገራት ሚና ትልቅ ሚና እንዳለውም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በባህልና ቱሪዝም እንዲሁም በተፈጥሮ ሃብት የበለጸገች ሀገር መሆኗን የገለጹት ሰብሳቢው በዚህም አጋጣሚ የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ መንግስት ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር እንደሚሰራም አብራርተዋል።

በ ሚፍታህ ኪያር

ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት

በፌስቡክ http://www.facebook.com/hoprparliament

በዩቲዩብ https://www.youtube.com/channel/UCZm9CZOqIyp8qesP3XkVBPg

በቴሌግራም https://t.me/ParlamaNews

በትዊተር http://twitter.com/fdrehopr

በዌብሳይት www.hopr.gov.et ይከታተሉ