አንድ ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውሉ የፕላስቲክ ከረጢቶች አካባቢን በመበከል ላይ መሆናቸው ተገለፀ

 (ዜና ፓርላማመጋቢት 17 2017 . የውሃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢ እና አካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከመንግሥትና የግል ዘርፍ ባለድርሻ አካላት ጋር በደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ረቂቅ አዋጅ ላይ ውይይት አድርጓል።

ደረቅ ቆሻሻ በአካባቢ እና በሰዎች ደህንነትና ጤና ላይ እያስከተለ ያለውን ተፅእኖ እና ጉዳት ለመከላከልና ለመቆጣጠር አዋጁ መዘጋጀቱ ተመላክቷል።

አዋጁ የደረቅ ቆሻሻ አሰባሰብ፣ አጓጓዝ፣ አከመቻቸት፣ መልሶ መጠቀም፣ መልሶ ዑደት እና አወጋገድ ሥርዓት ለመዘርጋት እንደሚያስችልም ተገልጿል።

ግለሰቦች የመኖሪያ አካባቢያቸውን እስከ 20 ሜትር ድርጅቶች እስከ 50 ሜትር የማፅዳት ኃላፊነት እንደሚጥልና አንድ ጊዜ ጥቅም ላይ ውለው የሚጣሉ የፕላስቲክ ከረጢቶች ምርት ረቂቅ አዋጁ እንደሚከላከል ተገልጿል።

ፕላስቲክን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩንና በዓመት በቢሊዮን የሚቆጠር ኃብት ማንቀሳቀሱን በዘርፉ የተሰማሩ ባለኃብቶች ገልጸዋል።

የፕላስቲክ ምርቶች በአግባቡ ከተያዙ ኃብት ናቸው፤  መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል ፕላስቲክን በማስወገድ የተሻለ ውጤት ተመዝግቧል የሚሉ ሀሳቦች ተሰንዝረዋል።

የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር / ለሊሴ ነሜ ረቂቅ አዋጁ አገር የጀመረችውን ፅዱና አረንጓዴ ኢትዮጵያን የመፍጠር እንቅስቃሴ የሚደግፍ መሆኑን ገልጸዋል።

ለአንድ ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውሉ የፕላስቲክ ከረጢቶች ለአሰባሰብ አዳጋች እና አካባቢን በመበከል  ማህበረሰቡን ለተለያዩ የጤና ችግሮች እየዳረጉ ስለሆነ መቆም አለባቸው ብለዋል።

የሚፈጠረው የሥራ ዕድል ጤናን የማይጎዳ ዘመናዊና ውጤታማ መሆን ይገባዋል ያሉ ሲሆን የበከለ ይክፈል መርሕን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የግል ዘርፉ ከትርፋማነት ጎን ለጎን የአካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ላይ ከመንግሥት ጋር በቅረበት እንዲሰራ ረቂቅ አዋጁ እድል እንደሚሰጥ አብራርተዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ / ፈቲያ አሕመድ ረቂቅ አዋጁ ረዥም ዘመናት ማገልገል እንዲችል በርካታ ባለድርሻዎችን ያካተተ ውይይት በቀጣይነት እንደሚደረግበት ገልጸዋል።

 ( በለጠ ሙሉጌታ)