አካታች ሃገራዊ መግባባት ለመፍጠር ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል - የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ

-------------------------

(ዜና ፓርላማ) መጋቢት 26 2017 .ም፤ አካታች ሃገራዊ መግባባት ለመፍጠር ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ ተናግረዋል፡፡

ህገ- መንግስትና ህገ መንግስታዊነት በሚል ርዕስ 3ኛው የፓርላማ የዜጐች ፎረም በኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተካሂዷል።

የውይይት መድረኩን በንግግር የከፈቱት የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ- ጉባኤ የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ ህገ- መንግስት የመንግስትንና የህዝብን የአስተዳደር ስርዓት የሚደነግግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ህገ መንግስቱ የሀገሪቱ የበላይ ህግ ነው ያሉት አፈ ጉባኤው ህዝብን በማሳተፍ የህገ መንግስቱ ባለቤት እንዲሆን ማስቻልና በጋራ በመመካከር መሻሻል ያለባቸው ቀሪ ስራዎች ላይ በመወያየት ሃገራዊ መግባባቱን ለማሳካት የጋራ መግባባት መፍጠር ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በዛሬው የውይይት መድረክ ህገ መንግስትና ህገ መንግስታዊነት፣ የህገ መንግስት ታሪክ በኢትዮጵያ፣ የህገ መንግስት ቅቡልነትና ተግዳሮት እንዲሁም የህገ መንግስት ሪፎርምና ሃገራዊ መግባባትን መሠረት ባደረጉ በሦስት ጥናታዊ ፅሁፎች ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት /ቤት ኃላፊ አቶ ትግሉ መለሰ እንደገለጹትም የህገ መንግስት ቅቡልነት እንዲኖር መሠረታዊ ችግሮችን በመለየት ሕዝቡ የህገ መንግስቱ ባለቤት እንዲሆን ህጋዊ ቅቡልነት፣ የማህበረሰብ ቅቡልነትና የሞራል ቅቡልነት እንዲኖር ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

አያይዘውም የሃገር መንግስቱ ትልቁ ሃሳብ ተቋማትን መገንባትና በህግ የተሰጣቸውን ተግባራት በማከናውን ለህዝቦች የተሻለ አገልግሎት መስጠት የሚችሉበት ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ማስቻል መሆኑን ገልፀዋል።

በሌላ በኩል ህገ መንግስቱን በልምምድ ማሳደግ እንደሚቻል ጠቁመው ህገ መንግስቱ ፍትሃዊ፣ የማህበረሰብ እሴቶችን ያገናዘበ ስለመሆኑ እንዲሁም በአወጣጥ ሂደቱ ያሉ ችግሮች በህገ መንግስቱ ቅቡልነት ላይ ያላቸው ተግዳሮቶች መታየት ያለበት ስለመሆኑ አብራርተዋል።

ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ህገ-መንግስት፣ ህገ-መንግስታዊነትና የህገ መንግስትን ታሪክ በኢትዮጵያ አስመልክቶ ባቀረቡት ሃሳብ የሌሎች ሃገራትን ተሞክሮ በማጣቀስ ኢትዮጵያ ከህገ- መንግስት በፍት በስርዓት ትመራ እንደነበር እና ወደ ዘመናዊ ስርአት ስንመጣም የኢትዮጵያ ህገ-መንግስት ስርአት እንዲሻሻል የደከሙ የሃገር ባለውለታዎች ናቸው ያላቸውን አንስተዋል።

የተከበሩ አቶ ዘካርያስ አረካሎ (ከህግና ፍትህ ጥናትና ምርምር ኢንስቲቲዩት) የህገ መንግስትና ሃገራዊ መግባባትን በሚመለከት ሃገራዊ መግባባቱን ከህገ መንግስቱ መሻሻል ጋር በማቀናጀት እና ከሌሎች ፍላጎቶች ጋር በማጣጣም ህገ መንግስቱ ረጅም ጊዜ እንዲያገለግል የማድረግ ሂደት ሊኖር እንደሚገባ ገልፀዋል።

አሁን ካለንበት ሁኔታ አንፃር አካታች ሃገራዊ መግባባት መፍጠር ያስፈልጋል ያሉት የተከበሩ አቶ ዘካሪያስ ለስኬቱም ሁሉንም ያካተተ ውይይት ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

የዕለቱ መድረክ አወያይ የነበሩት ዘሪሁን ይማም (/) ህገ መንግስትን ከማሻሻል በፊት ሃገራዊ መግባባት እንደሚያስፈልግ አንስተው ይህንንም ለማሳካት የተቋቋመው የምክክር ኮሚሽን ስራውን ሲያጠናቅቅ ህዝብን በማሳተፍ እና የተቋማትን ነፃነት በህገ- መንግስት በማክበር ኢትዮጵያ ወደ ህገ መንግስት ማሻሻል ከገባች ዘላቂና ለረጅም ጊዜ የሚያገለግል ህገ መንግስት ይኖራታል ሲሉ አስረድተዋል።

(በለምለም ብዙነህ)