ኢትዮጵያ መልካም የማይክሮ ኢኮኖሚ  አፈፃፀም ማስመዝገቧን ምክር ቤቱ ገመገመ

----------------------------

(ዜና ፓርላማ ) መጋቢት 8 2016 .ም፤ ኢትዮጵያ በማይክሮ ኢኮኖሚ መልካም  አፈፃፀም ማስመዝገቧን ምክር ቤቱ ገመገመ። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዘርፎች ዕቅድ አፈፃፀም የተሻለ አፈጻጻም እንዳለው ዛሬ የገመገመ ሲሆን ለምክር ቤቱ ቀጣይ የክትትልና ቁጥጥር ሥራ ወሳኝ ሚና እንዳለው ተጠቁሟል

የመንግሥት 2016  የስድስት ወራት  የዋና ዋና ዘርፎች ዕቅድ አፈፃፀም የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (/) ዛሬ ለምክር ቤቱ ያቀረቡ ሲሆኑ የዕቅድ አፈፃፀሙ ከቀድሞ የበለጠ መመዝገቡን ገልጸዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ   ከአጠቃላይ ኢኮኖሚው ማመንጨት ያለበትን ገቢ ከማመንጨት አኳያ ከታክስ ጋር ተያይዞ ያሉ ማሻሻያዎች ፀድቀው ወደ ሥራ በመግባት የመንግሥትን ገቢ ማሳደግ እንደሚገባ እና ለዚህም ምክር ቤቱ የበኩሉን እንዲወጣ አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ በማይክሮ ኢኮኖሚ በማህበራዊ ልማት በአስተዳደር፣ በሠላም እና በፍትሕ ዘርፎች ባለፉት ስድስት ወራት የተሻለ አፈፃፀም አስመዝግባለች ያሉት ሚኒስትሯ በግብርናው ዘርፍ የማዳበሪያ ስርጭት ፍትሐዊነትን ጨምሮ ምርታማነት፣ የኩታ ገጠም እርሻ ውጤታማነት እንዲሁም ትላልቅ እርሻና ኢንቨስትመንት ላይ ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ እንዲሁም የአምራች ኢንዱስትሪውን የማምረት አቅም ማሳደግ፣ የማዕድን አለኝታዎችን በመለየት ቴክኖሎጂ ላይ መዋለ ንዋይ ማፍሰስ "ኢንቨስት" ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ ጠቁመዋል።

በተያያዘ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር የተከበሩ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ  እንዳሉት የመንግሥት 2016  የስድስት ወራት  የዋና ዋና ዘርፎች ዕቅድ አፈፃፀም ለምክር  ቤት አባላት መቅረቡ በሀገራችን የሚከናወኑ የኢኮኖሚ ዕድገትና የልማት ሥራዎች  ያሉበትን ሁኔታ ከማሳወቅም ባሻገር በኢኮኖሚው፣ በማህበራዊ ልማት፣ በአስተዳደር፣ በፍትሕና በሠላም ዘርፎች የምክር ቤቱ አባላት መረጃ ኖሯቸው በብቃት የክትትልና ቁጥጥር የሚያደርጉባቸው ተቋማትን በተገቢው የመከታተልና መምራት እንዲችሉ የሚያግዝ እንደሆነ አንስተዋል።

አያይዘውም በቀጣይ የክትትልና ቁጥጥር ተግባራት እንዲሁም ሕጎች ሲወጡም ሆነ ሲረቀቁ የሚደረጉ ውይይቶች ምን ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለባቸው የሚያመላክት እንደሆነ ገልፀዋል

እንደ ተከበሩ የመንግሥት ተጠሪ አቶ ተስፋዬ ገለፃ እንደ መንግሥት ታክስ የመሰብሰብ አቅማችንን፣ መደበኛ ወጪ አጠቃቀማችንን፣ ኢንቨስትመንት እንዲሁም የብድርና ቁጠባ አቅማችን ላይ ትኩረት በመስጠት በተለይ የሥራ አጥነትን ችግር በመፍታት ረገድ የምክር ቤቱን ትኩረት የሚፈልጉ ጉዳዮች መኖራቸውን ከውይይቱ መረዳታቸውን ለአብነት ጠቁመዋል።

መንግሥት በሁሉም ዘርፍ ሪፎርም መጀመሩን የገለጹት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትሩ የሀገሪቷ የማይክሮ ኢኮኖሚ  መልካም አፈጻጸም ያለው መሆኑን ተናግረው  በበጀት ዓመቱ ኢኮኖሚያችን 7.9 እንደሚያድግ የሚጠበቅ እንደሆነ ጠቁመው፤ ለዚህም እንደመነሻ ያስረዱት ባለፉት 4 እና 5 አመታት በተሰሩት ሥራዎች የሀገሪቷ አጠቃላይ ምርት (GDP) በእጥፍ ማደጉን ነው ያስረዱት።

የኑሮ ውድነትን ለማሻሻል የተጀመሩ ሥራዎችን ውጤታማ ለማድረግ ሁሉም የምክር ቤት አባል በተሰማራበት ዘርፍ የድጋፍና ክትትል ስራውን በማጠናከር በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በሌላ በኩል ብልሹ አሰራርን በመዋጋት እና የሀብት ብክነትን በመቆጣጠር አሰራርን ማዘመን እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ እርምጃ በመውሰድ ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ሥራ ሊሠራ እንደሚገባም የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትሩ አፅንዖት በመስጠት ተናግረዋል