(ዜና ፓርላማ)፣ ሰኔ 29፣ 2015 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ በዓለም ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ ጥቂት ሀገራት ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት፤ ምክር ቤቱ ባካሄደው በ28ኛ መደበኛ ስብሰባው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው፡፡

ኢትዮጵያ ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት አንደኛ፤ ከሳብ ሰሃራ ሀገራት ሶስተኛ ደረጃ በመያዝ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገበች ያለች ሀገር መሆኗን መረዳት እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት በአይን የሚታይና በእጅ የሚዳሰስ በሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፎች ዕምርታዊ ለውጥ እያሳየ የመጣ እንደሆነ እና የግል ኢኮኖሚ ሴክተሩን በማነቃቃትም ተጨባጭ ለውጦችን ማምጣት መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል፡፡

የአንድ ሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት የሚለካበት አንዱ መመዘኛ ገቢና ወጪ ንግድ መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከገቢ ንግድ ጋር በተያያዘ 365.8 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘት እንደተቻለ እና ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር 26.1 በመቶ ዕድገት ማምጣት መቻሉን አስረድተዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት የውጭ ንግድ 574.5 ቢሊን ብር ወጪ እንደተደረገና ከባለፈው ዓመት አንጻር 13.4 በመቶው ለውጥ በመኖሩ በገቢና ወጪ መካከል ያለውን ልዩነት ማጥበብ መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመላክተዋል፡፡

ከኢኮኖሚ ጥገኝነት የወጣች ነጻ ሀገር መገንባት የሚቻለው የውስጥ ገቢን በማሳደግና ወጪን በመቀነስ በመሆኑ ሁሉንም ዜጋ የሀገር ውስጥ ገቢን ለማሳድ የድርሻውን መወጣት እንዳለበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል፡፡

በወጪ ንግድ ቡና፣ ጫት፣ ወርቅ እና ማዕድን 11 በመቶ የቀነሰውን ንግድ ለማካካስ በተሰራው ስራ በስንዴ፣ በአልባሳት፤ በድንጋይ ከሰል እና በአገልግሎት ዘርፉ በውጭ ንግድ ገቢ የተሻለ ውጤት ማምጣት መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡

የዋጋ ግሽበቱ ዓለም አቀፋዊ ቢሆንም፤ በገበያ ላይ የተረጨውን ገንዘብ በመቆጣጠር አቅርቦትን እና ፍላጎትን ለማጣጣም በተሰራው ስራ የኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት 30 በመቶ መቀነስ መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት በግብርናው ዘርፍ 6.3 በመቶ እና በኢንዱስትሪው ዘርፉ 8.2 በመቶ ዕድገት እንደሚጠበቅ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመው፤ በአገልግሎት ዘርፉ በቱሪዝም፣ በአየር መንገድ እና በፋይናንሽያል ሴክተሩን ጨምሮ በአጠቃላይ ከ7.5 በመቶ ያላነሰ የኢኮኖሚ ዕድገት በኢትዮጵያ እንደሚመዘገብ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመላክተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የዕዳ ጫናዋ ከለውጥ በፊት 59 በመቶ እንደነበር እና አሁን ላይ የዕዳ ጫናን ለመቀነስ ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራቱ የሀገሪቱን የዕዳ ጫና 38 በመቶ ማድረስ እንደተቻለ እና ለቀጣይ ሶስት ዓመታት 30 በመቶ የዕዳ ጫናን ለመቀነስ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የማይክሮ ኢኮኖሚ ስብራቶችን በመጠገን፣ ማረቅና ማሻሻል እንዲሁም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የሀገርን እድገት ለማስቀጠል በትኩረት ታቅዶ በመስራቱ ዕምርታዊ ለውጥ ማምጣት መቻሉን ለምክር ቤት አባላት አስረድተዋል፡፡

በ መኩሪያ ፈንታ 

ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት፡- 
በፌስቡክ http://www.facebook.com/hoprparliament 
በዩቲዩብ https://www.youtube.com/@FDREHOPR 
በቴሌግራም https://t.me/ParlamaNews 
በትዊተር http://twitter.com/fdrehopr 
በዌብሳይት www.hopr.gov.et ይከታተሉ