ጥቅምት 19 ቀን 2015 ዓ.ም፣ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ ከሞዛምቢክ ሪፐብሊክ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የተከበሩ ሆፕ ላውሪን ፍራንሲስኮ ንሂዋን ጋር ሰሞኑን በሞዛምቢክ ተገኝተው ውይይት አድርገዋል።

በውይይቱ በሽብርተኝነት፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በሰላም እና ደህንነት ዙሪያ ባሉ ተግዳሮቶች በትብብር መስራት አስፈላጊነቱ ላይ በትኩረት መክረዋል፡፡

የሁለቱ ሀገራት አፈ-ጉባኤዎች በየሀገራቸው ስላለው ተጨባጭ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ከተወያዩ በኋላ፤ የሁለቱን ምክር ቤቶች አጋርነትን ለማጠናከር ተስማምተዋል።

የአፍሪካ የጋራ አጀንዳዎችን እንደ የአፍሪካ፣ የካረቢያን እና የፓስፊክ ሀገራት ቡድን (ACP-EU) እንዲሁም የአውሮፓ ህብረት ባሉ መድረኮች ላይ ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው ለማድረግ በቁርጠኝነት ለመስራትም ተስማምተዋል።

የተከበሩ አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ፤ አፍሪካዊ ጉዳዮች በዓለም አደባባይ ጎልተው እንዲወጡ ኢትዮጵያ ዝግጁ እንደሆነች አረጋግጠው፤ ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄዎችን የማፈላለግ አስፈላጊነት ላይ አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።

በተጨማሪም አፈ-ጉባኤ ታገሰ የሞዛምቢክ ሪፐብሊክ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆፕ በቅርቡ የአፍሪካ፣ የካሪቢያን እና የፓሲፊክ ሀገራት ፓርላሜንታዊ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው በመመረጣቸው የእንኳን ደስ አልዎት መልዕክት አስተላልፈዋል።

በተከበሩ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ የሚመራ ልዑክ በ61ኛው የአፍሪካ፣ የካሪቢያን እና የፓሲፊክ ሀገራት የፓርላማ ጉባኤ እና በ42ኛው የአፍሪካ፣ ካረቢያን እና ፓስፊክ ሀገራት እና የአውሮፓ ህብረት የጋራ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ በሞዛምቢክ ማፑቶ ተገኝተዋል።

ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት

በፌስቡክ http://www.facebook.com/hoprparliament

በዩቲዩብ https://www.youtube.com/watch?v=cp_8F5TEeFE

በቴሌግራም https://t.me/ParlamaNews

በትዊተር http://twitter.com/fdrehopr

በዌብሳይት www.hopr.gov.et ይከታተሉ