ኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ተወያዩ

(ዜና ፓርላማ)፤መጋቢት 13/2013 ዓ/ም.፤ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ጀምስ ፒታን ጋር የሁለቱን አገሮች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ተወያይተዋል፡፡

አምባሳደሩን በቢሮአቸው ተቀብለው ያነጋገሩት ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ኢትዮጵያ የሁለቱን ሀገራት መልካም ግንኙነት ለማጎልበት በንግድና ኢኮኖሚ፣ በመሰረተ-ልማት፣ በኢንቨስትመንት እና በጸጥታው ዘርፍ ከደቡብ ሱዳን ጋር ትኩረት ሰጥታ መስራት እንደምትፈልግ አስረድተዋል፡፡

ወንጀልን በጋራ በመከለላከል የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን የበለጠ ለማሳደግ ሁለቱ ሀገራት በትኩረት መስራት እንዳለባቸውም ዶ/ር ነገሪ አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የናይል ተፋሰስ ሀገራትን በማይጎዳ መልኩ ህዳሴ ግድቡን እየገነባች እና ተፈጥሮአዊ መብቷን ለመጠቀም ጥረት እያደረገች መሆኑን የገለጹት ዶክተር ነገሪ ሱዳን እና ግብጽ የሚያነሱትን ቅሬታ በሰላማዊ ድርድር ለመፍታት ዝግጁ መሆኗን ጠቁመዋል፡፡

የህዳሴ ግድቡ ግንባታ ከተጠናቀቀ በኋላ የሚያመነጨው ኃይል ለምስራቅ አፍሪካ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው የአመላከቱት ዶ/ር ነገሪ፤ ግድቡ የኢትዮጵያ እና የደቡብ ሱዳን ገጠራማ አካባቢዎችን በኤሌክትሪክ ተደራሽ እንደሚያደርግ ተስፋ ተጥሎበታልም ብለዋል፡፡

ዶ/ር ነገሪ አክለውም በህዳሴ ግድቡም ሆነ በኢትየጵያ እና በሱዳን መካከል የሚስተዋለውን የድንበር ይገባኛል ውዝግብ በሰላማዊ ድርድር ለመፍታት መንግስት ሁለንተናዊ ጥረት እያደረገ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ 

የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል የተከበሩ አቶ ወርዶፋ በቀለ በበኩላቸው ህዳሴ ግድቡ የሱዳንንም ሆነ የግብፅን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል ሳይሆን ጥቅሙ የጎላ እንደሆነ አንስተው በሌላ በኩል ኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን ያላቸውን ሁለንተናዊ ግንኙነት የበለጠ ማሳደግ እንዳለባቸው ነው ያሳሰቡት፡፡

በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ጀምስ ፒታ በበኩላቸው ሱዳን እና ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ መልካም ግንኙነት እንደነበራቸው ገልጸው፤ ለአብነትም ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት ሱዳን ከኢትዮጵያ ጎን እንደነበረች አስታውሰዋል፡፡

ደቡብ ሱዳን እንደ አገር ስትመሰረትም ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር የበኩሏን ድጋፍ ማድረጓን ያስታወሱት አምባሳደር ጀምስ፣ አሁንም ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን ተማሪዎች ስኮላርሺፕ በመስጠጥና ፖሊስ በማሰልጠን ድጋፍ እያደረገች መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አገራቸው በሁለቱ አገራት ድንበር አካባቢ ወንጀልን በጋራ ለመከላክል እና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ደቡብ ሱዳን ውስጥ ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ቪዛ እየሰጠች መሆኑንም አምባሳአደሩ ገልጸዋል፡፡  

በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ ሱዳን እና ግብፅ የሚያሳዩት ተቃውሞ እና አለመግባባት በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት መፈታት እንዳለበት እና ኢትዮጵያም ጥቅሟን ለማስከበር ለድርድሩ ዝግጁ መሆን እንዳለባት አምባሳደር ጀምስ አሳስበዋል፡፡