በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ የግጭት ተጋላጭነትን በመቀነስ በሀገራዊ ጉዳዮች ብሔራዊ መግባባት ላይ እንዲተኮር አሳሰበ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ማሳሰቢያውን የሰጠው፤ የኢፌዴሪ የሰላም ሚኒስቴርን የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሰሞኑን በገመገመበት ወቅት ነው፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ዲማ ነገዎ (ዶ/ር) በግምገማው ወቅት እንዳስገነዘቡት፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የግጭት አፈታት ሥርዓቱን በመከለስ፣ የግጭት መንስዔዎችን በመለየት፣ በየቦታው የሚከሰቱ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን ለመከላከል፤ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መሥራት ይኖርበታል፡፡

ሰብሳቢው አያይዘውም፤ በሀገራችን የሚስተዋለው የሰላም እጦት ውስብስብ ከሆኑ ጉዳዮች ስለሚነሳ፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ግጭቶች ሳይባባሱ እና የከፋ ጉዳት ሳያስከትሉ ተጋላጭነትን ለመቀነስ መሥራት አለበት ብለዋል፡፡ በተለይ ለግጭት ተጋላጭ በሆኑ አከባቢዎች መንስዔዎችን በማጥናት በልዩ ትኩረት እንዲሠራ አሳስበዋል - ዶክተር ዲማ ነገዎ፡፡

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የዜጎችን ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ከማረጋገጥ አኳያ ብዙ እንደሚጠበቅበት በቋሚ ኮሚቴው አባላት የተመላከተ ሲሆን፤ ማኅበራዊ እና ባሕላዊ ትውፊቶቻችንን በመጠቀም፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎች እና ዕሴቶች ላይ የጋራ ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋልም ተብሏል፡፡

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በኃይማኖት እና በብሔር ጽንፈኝነት የሚነሱ ችግሮችን ለመከላከል እና በክልሎች መካከል በመግባባት እና በአጋርነት ላይ የተመሠረተ መልካም ግንኙነት እና ትብብር እንዲጎለብት፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባም ቋሚ ኮሚቴው አስገንዝቧል፡፡

የኢፌዴሪ የሰላም ሚኒስትር አቶ ብናልፍ አንዷለም የዕቅድ አፈጻጸምን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ፤ ሰላም የብዙ አካላትን ተሳትፎ የሚጠይቅ መሆኑን አመላክተዋል፡፡ በማኅበራዊ መገናኛ መንገዶች የሚለቀቁ መረጃዎች እንኳን በሰላማችን ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እየፈጠሩ ቢሆንም፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ግን አስተዋይ በመሆኑ ችግሮችን ሊቋቋማቸው ችሏል ብለዋል፡፡

ሚኒስትሩ አክለውም፤ የኃይማኖት ተቋማት መሠረታቸው ሰላም በመሆኑ የችግሩ መንስዔ እንዳልሆኑ ጠቅሰው፤ ነገር ግን አንዳንድ የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው አካላት አንዱ በሌላው ላይ እንዲነሳ እየጣሩ እንደሚገኙ የአደባባይ ሚስጥር ሆኗል ብለዋል፡፡

ከሀገረ-መንግስት ግንባታው ጋር ተያይዞ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በትውልድ ግንባታው ረገድ የተጀመሩ ሥራዎችን አጠናክሮ በመቀጠል፣ የበጎ ፍቃድ አገልግሎትን በማስፋት፣ በክልሎች መካከል ጤናማ ግንኙነት እንዲኖር፣ የግጭት ስጋት ያለባቸውን ቦታዎች በጥናት ለይቶ እየሠራ እንደሆነ፤ ከተቋሙ ያገኘናቸው መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡