የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ ግጭቶች ከመከሰታቸው በፊት ለግጭት ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች እና ሁኔታዎች ላይ ጥናት እንዲደረግ አሳሰበ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ማሳሰቢያውን የሰጠው፤ በዛሬው ዕለት የሰላም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤትን የሥራ እንቅስቃሴ ተዘዋውሮ ከተመለከተ በኋላ በሰጠው አቅጣጫ ነው፡፡ በወቅቱም ከሪፖርት ባለፈ በተቋሙ ያለውን ሁኔታ ተመልክቷል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ዲማ ኖጎ (ዶ/ር)፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባለፉት ሃያ እና ሠላሳ ዓመታት የነበሩ ግጭቶች ምንጮቻቸውን እና የአፈታት ሥርዓታቸውን በማጥናት ላይ ትኩረቱን ማሳረፍ እንደሚገባው አስገንዝበዋል፡፡

አያይዘውም፤ በሀገራችን የተለያዩ ባሕላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓቶች እንዳሉ አስታውሰው፣ የግጭት አፈታቶቹ ምን ያህል ውጤት አምጥተዋል በሚለው ላይም ሊጠና ይገባል ብለዋል፡፡

በተቋሙ የሰላም ኤግዝቢሽን ማዕከል የጋሞ አባቶችን ነባር እና ባሕላዊ የዕርቀ-ሰላም መንገድ የሚያሳየውን፤ ተንበርክከው በሰው እና በንብረት ላይ ሊደርሱ የሚችሉትን አደጋዎች ያስቀሩበትን የአባቶች ተማጽኖ ተምሳሌታዊ ምስል እንዲሁም የኢትዮጵያ የሰላም እናቶችን ምስለ-ተማጽኖ ማየታቸውን፣ የቋሚ ኮሚቴው አባላት አድንቀዋል፡፡ ማዕከሉን ማጠናከር ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡

ተቋሙ በዘመናዊ አደረጃጀት ተልዕኮውን ለመፈጸም በሚያስችል ቁመና ላይ እንዳለ የተረዳ መሆኑን የጠቆመው ቋሚ ኮሚቴው፤ ግጭቶች ከመከሰታቸው በፊት የመከታተያ ዘዴ በቴክኖሎጂ መደገፉ ጥሩ ነው ብሏል፡፡ ነገር ግን ሕዝቡ በዚህ ዘዴ መንግስትን እንዲያግዝ የሚያደርግ የአሠራር ሥርዓት ዘርግቶ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚያስፈልግ ጠቁሟል፡፡

አክሎም፤ በተለያዩ የምክክር መድረኮች መፍትሔ ያመጡ እና ለሰላም ዋጋ የከፈሉ አካላትም በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ኤግዚቢሽን ማዕከል ሊታወሱ እንደሚገባ ጥቆማ ሰጥቷል፡፡

በሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታ እና ብሔራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደአ በበኩላቸው፤ በተቋሙ አዲስ የተሠራው አደረጃጀት ዕውቀትን መሠረት ያደረገ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በፈተና በቂ ውጤት ያመጡት ብቻ በአዲሱ ምደባ መካተታቸውን እና የሥራ መደቦችም ከ6 መቶ 48 ወደ 2 መቶ 73 ዝቅ ማለታቸውን ተናግረዋል፡፡

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ግጭቶች ከመከሰታቸው በፊት መከላከል የሚያስችሉ ሥርዓቶችን ዘርግቶ እየሠራ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በግጭት አፈታት ዙሪያ ከክልሎች እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትኩረት የምንሠራ ይሆናል ብለዋል፡፡

አያይዘውም፤ ከበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ጋር ተያይዞ አጠቃላይ የመጣንበት የትምህርት ሥርዓት ያስከተለውን የአስተሳሰብ ሁኔታ መቀየር እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል፡፡