(ዜና ፓርላማ)፤ ሕዳር 13፣ 2015 ዓ.ም፤ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 5ኛ መደበኛ ስብሰባው የኢፌዴሪ የመከላከያ ስራዊት አዋጅ ለማሻሻል ለምክር ቤቱ በቀረበበት ወቅት ራሱን የቻለ የመከላከያ አዋጅ ሊወጣ እንደሚገባ የምክር ቤት አባላት ጠቁመዋል፡፡

ለሀገር አለኝታ የሆነው የኢትዮጵያ መከላከያ ስራዊትን ክብር የሚመጥን የደመወዝና የካሳ ክፍያ እንዲሁም ሌሎች ጥቅማ-ጥቅሞች በሚገባ እንዲከበሩ ራሱን ችሎ የመከላከያ አዋጅ ቢወጣ ፋይዳው የጎላ እንደሆነ የምክር ቤት አባላት አመላክተዋል፡፡

የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር የተከበሩ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ የመከላከያ ሰራዊት አዋጅ እንዲሻሻል ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት በአዋጅ ማሻሻያው እንዲካተቱ ትኩረት ከተሰጠባቸው አበይት ጉዳዮች መካከል ከጡረታ መውጫ እድሜ ጣሪያ አወሳሰንና የጡረታ እድሜ ከማራዘም ጋር በተገናኘ፣ ከስራዊት መብትና ጥቅማ-ጥቅሞች አንጻር መታየት ያለባቸውን ጉዳዮች በተመለከተ እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡

በተመሳሳይም የሀገርን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል ጦርነት ሲከሰት የሰራዊት አባል የነበሩትን መልሶ ከመቅጠር ጋር በተገናኘ ስለሚኖረው አፈጻጸም፣ ስለብሔራዊ አገልግሎት፣ ሌሎች የአፈጻጸም ክፍተት ያለባቸውን ጉዳዮች ለማስተካከል የአዋጁ መሻሻል አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትሩ አቶ ተስፋዬ ለምክር ቤቱ አብራርተዋል፡፡

የመከላከያ ሰራዊት አባላት ጡረታ ከወጡ በኋላ ሰራዊቱን በተለያዩ የሙያ ዘርፎች እንዲያገለግሉ ራሱን የቻለ የመከላከያ ሰራዊት ምክር ቤት ሊቋቋም እንደሚገባም ከምክር ቤት አባላት አስተያየት ተሰጥቷል፡፡

የመከላከያ ሰራዊቱን መብትና ግዴታዎች፣ የጡረታ መውጫ ጊዜና ጥቃማ-ጥቅሞች እንዲከበሩለት አዋጁ የሚመራለት ቋሚ ኮሚቴ በአጽንኦት ሊመለከተው እንደሚገባ የምክር ቤት አባላት አሳስበዋል፡፡

ምክር ቤቱ የመከላከያን ረቂቅ አዋጅ ውሳኔ ቁጥር 9/2015 በማድረግ በአንድ ድምጸ-ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ ለዝርዝር እይታ ለውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል፡፡

በተመሳሳይም ምክር ቤቱ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋምን እንደገና ለማቋቋም የወጣውን አዋጅ ለማሻሻል በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ በሰፊው ከተወያየበት በኋላ በሙሉ ድምጽ ለዝርዝር እይታ ለህግ፣ ፍትህ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል፡፡

ምክር ቤቱ በዛሬ ውሎው የገቢዎች ሚኒስቴር ሚኒስትር የክብርት አይናለም ንጉሴን ሹመት መርምሮ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡

በ ተስፋሁን ዋልተንጉስ

ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት 
በፌስቡክ http://www.facebook.com/hoprparliament 
በዩቲዩብ https://www.youtube.com/channel/UCZm9CZOqIyp8qesP3XkVBPg
በቴሌግራም https://t.me/ParlamaNews 
በትዊተር http://twitter.com/fdrehopr 
በዌብሳይት www.hopr.gov.et ይከታተሉ