(ዜና ፓርላማ)፤ መስከረም 11፣ 2015 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የጤና ማህበራዊ ልማት፣ ባህል እና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች በሀገራችን እየተከሄደ ያለውን ሁለንተናዊ ለውጥ በተመለከተ ከአውሮፓ ህብረት የፓርላማ አባላት ጋር በወቅታዊ እና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ውይይት አድርገዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት አፈ-ጉባኤውን ጨምሮ፤ የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች፤ በጀትና ፋይናንስ እና የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህል እና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች ገለጻ አድርገዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ የኢትዮጵያ መንግስት በሁለንተናዊ ዘርፎች በርካታ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝና ሀገራችን እያጋጠማት ያለውን ችግር ለመፍታት ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በማቋቋም እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የተከበሩ አፈ-ጉባኤ አክለውም፤ የኢትዮጵያ መንግስት ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ያለውን ፍላጎት ወደኋላ በመተው አሸባሪው ህውሓት ያወጣውን ሕገ-መንግስት በመፃረር ጦርነት በራሱ ፍላጎት ያስጀመረው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በ21ኛው ክፍለ-ዘመን ጦርነት አስፈላጊ ባለመሆኑ የሩሲያና የዩኩሬን ችግሮቻቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት እንዳባቸውና አውሮፓ ህብረትም የበኩሉን እገዛ እንዲያደርግላቸው ሲሉ የተከበሩ አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ አክለው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ለአየር ንብት ትኩረት ሰጥቶ በመስራት በዓመቱ 4.5 ቢሊዮን ችግኝን መትከል መቻሉን አፈ-ጉባኤው ጠቁመዋል፡፡

የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ዲማ ነገዎ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ አሸባሪው ህወሓት በድጋሜ በከፈተው ጦርነት በአማራና በአፋር ክልሎች ኢ-ሰብአዊ ድርጊት እየፈጸመ እንደሆነና ለትግራይ ሕዝብ የሚላከውን የሰብዓዊ ድጋፍ ለጦርነት እያዋለ እንደሆነና የኢትዮጵያ መንግስት ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የጤና ማህበራዊ ልማት፣ ባህል እና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ ወርቅሰሙ ማሞ በበኩላቸው፤ መንግስት የሴቶችን ተሳትፎ በተግባር በማረጋገጥ በምክር ቤቱ 42 በመቶው እንዲሁም የሴቶችን የካቢኔ ተሳትፎ 50 በመቶ መድረሱን አስረድተዋል፡፡

አሸባሪው ህወሐት በከፈተው ጦርነት አስቸኳይ ድጋፍ የሚሹ 5 ሺህ 5 መቶ 67 ሴቶችና ህጻናት በመኖራቸው ለጤና፤ እና ሴቶችና ማህበራዊ ሚኒስቴር ድጋፍ እንዲደረግላቸው እየተሰራ መሆኑን የተከበሩ ወ/ሮ ወርቅሰሙ ማሞ ገልጸዋል፡፡

በሀገራችን በጦርነቱ ምክንያት 4.8 ሚሊዮን ዜጎች እንደተፈናቀሉ እና በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች በድርቅና በጎርፍ የታጎዱ ዜጎች በመኖተራቸው የአውሮፓ ህብረት አስፈላጊውን የሰብአዊ እርዳታ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ሰብሳቢዋ ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስትና ሕዝቦች ሰላም ወዳድ መሆናቸውን ያለውን እውነታ ለዓለም እንዲያሳውቁ ሲሉ ለአውሮፓ ህብረት የፓርላማ አባላትን አበክረው ጠይቀዋል፡፡

የአውሮፓ ህብረት መንግስት ለኢትዮጵያ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ በፋይናንስ፣ በስልጠና እና በልምድ ለውውጥ ዘርፎች አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርግላቸው የተከበሩ ወ/ሮ ወርቅሰሙ ጠይቀዋል፡፡

የአውሮፓ ህብረት የፓርላማ አባላት ለተደረገላቸው ማብራሪያ አመስግነው፤ የኢትዮጵያ መንግስት እያደረገው ላለው ሁለንተናዊ ለውጥ እና የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ያለውን ቁርጠኝነት አድንቀዋል፡፡

በሴቶች ኮከስ የሴቶችን ችግር ለመፍታት እየሰራ ያለው ስራ እና የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ለመቋቋም መንግስት እየሰራቸው ያሉ ስራዎችን የሚበረታቱ መሆናቸውን የአውሮፓ የፓርላማ አባላት ተናግረዋል፡፡

የኢትትዮጵያ መንግስት የሚፈጠሩ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት የሚያደርገውን ጥረት እንደሚደግፍ እና የሰብአዊ ዕርዳታ እንዳይደርስ የሚያደርጉ እንቅፋቶችን በጋራ እንደሚሰሩ የአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ገልፀዋል።

በ መኩሪያ ፈንታ

ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት
በፌስቡክ http://www.facebook.com/hoprparliament
በዩቲዩብ https://www.youtube.com/watch?v=cp_8F5TEeFE
በቴሌግራም https://t.me/ParlamaNews
በትዊተር http://twitter.com/fdrehopr
በዌብሳይት www.hopr.gov.et ይከታተሉ