የሲዳማ ክልል ለሰላም መረጋገጥ የሚያደርገው ጥረት በተሞክሮነት የሚወሰድ መሆኑን ኮሚቴው ገለጸ

(ዜና ፓርላማ) ሚያዚያ 7/2013 ዓ.ም፤ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ከኦሮሚያ እና ከደቡብ ክልሎች ጋር ያለውን ሰላማዊ ግንኙነት ለማጠናከር የሚያደርገው ጥረት በተሞክሮነት የሚወሰድ መሆኑን ገልጿል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ይህን የገለጸው ሰሞኑን መክልሉ ባደረገው የመስክ ምልከታ ወቅት ሲሆን ክልሉ የኅብረተሰቡን ሰላም እና ደህንነት ለማረጋገጥ እንዲሁም ልማታዊ እንቅስቃሴዎች በጸረ-ሰላም ኃይሎች እንዳይደናቀፉ ለማድረግ ከአጎራባች ክልሎች ጋር እያከናወናቸው የሚገኙ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብሏል፡፡

የቋሚ ኮሚቴ አባል የተከበሩ አቶ ቡንጡቃ ዋሬ የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ የክልሉን ልማት ከማረገጥ እንዲሁም ዜጎች በብሔራቸውና በዕምነታቸው ምክንያት ሳይሸማቀ ከየትኛውም የፀጥታ ስጋት ነጻ ሆነው በክልሉ ተንቀሳቅሰው ሀብት የማፍራት ህገ-መንግስታዊ መብታቸው እንዲከበር ከአጎራባች ክልሎች ጋር እየሰራ ያለው የተቀናጀ ሥራ ለሌሎችም ተሞክሮ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።

የተከበሩ አቶ ሻምበል ነጋሳ በበኩላቸው ሀገሪቱ በአሁኑ ስዓት የጀመረችውን የለውጥ እንቅስቃሴ ከግብ እንዳይደርስ ለማደናቀፍ፣ ዜጎች በአብሮነትና በአንድነት መኖር የማይዋጥላቸውና ህልውናቸው ዜጎችን በመረበሽ፣ በመግደል እና በማፈናቀል ላይ የተመሰረተ ጸረ-ሰላም ቡድኖችን ከመከላከል እና እርምጃዎችን ቀድሞ ከመውሰድ አንፃር እንዲሁም በመንግሥት መዋቅር ስር የተሰገሰጉ ኪራይ ሰብሳቢዎችን ክልሉ ወደ ህግ ማቅረቡ የሚያበረታታ ነው ብለዋል፡፡

የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የሰላምና የጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዎስ በበኩላቸው በክልሉ የሚገኙ ኅብረ-ብሄራዊነትን አንግው የሚሰሩ ተቋማት  በህብረተሰቡ ተዓማኒና ግልጽ እንዲሆኑ ለማስቻል ሁሉም የክልሉ ባለድርሻ አካላት ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያደርጉ ጠቁመው ይህንንም ክትትል በበለጠ ለማዘመንና ለማሻሻል በቅርቡ በተቋማቱ ላይ የደህንነት ካሜራዎችን ለመግጠም እየተዘጋጁ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በክልሉ እየታየ ያለው መረጋጋትና ሰላማዊ እንቅስቀሴ ያልተጠላቸው ጸረ-ሰላም ኃይሎች ዛሬም በክልሉ እንዳሉ ጠቅሰዋል፡፡

የጸጥታ አካላት ህብረተሰቡ ጋር ተቀናጅተው ባደረጉት የጋራ እንቅስቃሴ በዚህ ዓመት ብቻ ለጥፋት ዓላማ ይውል የነበረ 10,000 ጥይት፣ 150 ሽጉጥ2 ብሬን፣ 1000 የብሬን ጥይት፣ 13 ክላሽ፣ 54 ቦምብ እና 10 የጦር ሜዳ መነጽር እንዲሁም ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ህገ-ወጥ የኮንትሮባንድ ንግድ እቃዎችን በቁጥጥር ስር እንዳዋሉም  አቶ አለማየሁ ተናግረዋል፡፡

ሲዳማ ብሔራዊ ክልል ላይ ማንኛውም ዜጋ በነጻነት ተንቀሳቅሶ ሀብት የማፍራት እና የመደራጀት ሙሉ መብት አለው ያሉ ሲሆን ይህንንም ተልዕኮ ለማሳካት የክልሉ መንግስት በቁርጠኝነት አበክሮ እንደሚሰራም ነው አክለው ያብራሩት፡፡

በሚፍታህ ኪያር