Kemal Hashi Muhammed

የተከበሩ አቶ ከማል ሃሺ ሙሃመድ

Biography

የተከበሩ ከማል ሃሺ መሐሙድ፤ የሀገራችንን የፖለቲካ ምኅዳር በቅርቡ ከተቀላቀሉት ወጣት፣ ባለዕምቅ ጉልበት እና ተስፋ ከሚጣልባቸው ፖለቲከኞች አንዱ ናቸው። በአሁኑ ጊዜም የ6ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆነው፤ የተሰጧቸውን ተጨማሪ የሕዝብ እና የመንግስት ኃላፊነቶች እየተወጡ ይገኛሉ። የሕይወት ጉዟቸው እንደሚያመላክተው፤ የተከበሩ ከማል ሃሺ ከሕብረተሰቡ ጋር በነበራቸው መስተጋብር የተለያዩ አስተዋጽዖዎችን አበርክተዋል። ለማኅበራዊ ፍትሕ፣ ለተሟላ ሰላም እንዲሁም ለሁሉ-አቀፍ ዙሪያ-መለስ ልማት መረጋገጥ ያደረጉት እንቅስቃሴ፤ ከግለሰባዊ ማንነታቸው ተዳምሮ ለደረሱበት የፖለቲካ ደረጃ እንዳበቃቸውም ይታመናል። እንደዚሁም በመገናኛ ብዙኃናት፣ በተግባቦት ዘርፎች፣ በዓለም-አቀፍ ግንኙነቶች፣ በከፍተኛ ትምህርት ረገድ እንዲሁም በሥራ ፈጠራ እና በጎ ፈቃደኝነት ሥራዎች ያሳዩት የሙያ እና የኃላፊነት ትጋት፤ አሁን ለደረሱበት ደረጃ ተጨማሪ ዓቅም እንደሆነላቸው መገንዘብ ይቻላል። የተከበሩ ከማል ሃሺ ተለይተው በሚታወቁበት በበጎ ፈቃደኝነት ዘርፍ፤ በርካታ የበጎ ፈቃድ ተግባራትን ጠንስሰው እና መርተው አከናውነዋል። ይህንንም የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ከነበሩበት እስከ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ሕይወታቸው ይዘውት መምጣታቸውን ታሪካቸው ይመሰክራል። ዳሩ ግን በኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማኅበር፣ በተማሪዎች ሕብረት እና በተለያዩ የተማሪዎች የክለብ አደረጃጀቶች የነበራቸው የጎላ ተሳትፎ፤ ከሌሎቹ ገዝፎ ይታያል። ይሁን እንጂ በትምህርት እና በልማታዊ ተግባቦት ዘርፎች ያሳረፏቸው የሥራ ፈጠራ አሻራዎች እንደዚሁ በቀላሉ የሚታለፉ አለመሆናቸው ልብ ሊባል ይገባል። ከተጠቀሱት ግለሰባዊ አሻራዎች ባሻገር፤ የተከበሩ ከማል ሃሺ በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የመገናኛ ብዙኃን እና የተግባቦት የትምህርት መስኮች መምህር ሆነው አገልግለዋል። ይህም የሕብረተሰቡን ባሕል እና ወግ ጠለቅ ብለው እንዲመራመሩ ዕድል ሰጥቷቸዋል። በዝርዝር ሲታይ፤ የተከበሩ ከማል ሃሺ በጅግጅጋ ኤፍ ኤም የሬዲዮ ስርጭት፣ በሶማሌ ቴቪ፣ በኢቢሲ እና በፎርቹን ጋዜጣ በሙያተኛነት እና በኃላፊነት ሠርተዋል። በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ በነበሩበት ወቅትም፤ በኤክዘኪዩቲቭ ዳይሬክተር ማዕረግ የፕሬዚዳንቱ አማካሪ፣ የዓለም-አቀፍ ግንኙነት እና ትብብር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር እንዲሁም የኮርፖሬት ተግባቦት እና የገበያ ጥናት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሆነው የበኩላቸውን ድርሻ ተወጥተዋል። እንደዚሁም ክልል-አቀፍ በሆኑ የሲቪክ ማኅበራት ዘንድ እና በአሜሪካ የተራድኦ ድርጅት ፕሮጄክቶች፤ የማኅበራዊ ባሕርይ ለውጥ እና ተግባቦት እንዲሁም የማኅበራዊ ግብይት ልዩ ባለሙያ ሆነው አገልግለዋል። በትምህርት ዝግጅት ረገድ የሁለተኛ ዲግሪ ባለቤት የሆኑት የተከበሩ ከማል ሃሺ፤ በመገናኛ ብዙኃን፣ በተግባቦት፣ በሕግ እና በስነ-ልቦና የትምህርት ዓይነቶች የማይናቅ ዕውቀት አላቸው። ከዚህም በላይ በሀገር-አቀፍ እና ዓለም-አቀፍ ደረጃዎች በተካሄዱ የተለያዩ ጉባዔዎች በመሳተፍ ልምዶችን አካብተዋል። በዚህ ረገድ በተለይ በአሜሪካ ሀገር ኢትዮጵያን ወክለው በዓለም-አቀፍ የጎብኚዎች የአመራር ስልጠና መርኃ-ግብር በመሳተፍ ያገኙት ተሞክሮ፤ የዘመናዊውን ዓለም አሁናዊ ክስተቶች በተሻለ እንዲገነዘቡ ረድቷቸዋል። የተከበሩ ከማል ሃሺ፤ በጽሑፉ መግቢያ እንደተመላከተው በአሁኑ ወቅት የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች የ6ኛው ምክር ቤት አባል ናቸው። በአላቸው ዘርፈ-ብዙ ልምድ መንስዔም የ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አማካሪ ኮሚቴ አባል ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ። በተጨማሪም ምክር ቤቱ ተልዕኮውን ለማሳካት እንዲረዳው በሚያቋቁማቸው ልዩ የኮሚቴ አደረጃጀቶች እየተሳተፉ፤ ሀገራዊ እና ሕዝባዊ አደራቸውን በመወጣት ላይ ናቸው።

Intervention of the Member

votes.