የትራንስፖርት ዘርፉን ድክመቶች መለየት በሚያስችል መልኩ ታቅዶ መስራት እንዳለበት ተጠቆመ

(ዜና ፓርላማ)፣ግንቦት 09/09/2013 ዓ.ም.፤ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ ልማት፣ ኮንስትራክሽንና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የትራንስፖርት ዘርፉን ድምክመቶች መለየት በሚያስችል መልኩ ታቅዶ መስራት እንዳለበት አሳስቧል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ይህን ያሳሰበው ዛሬ የትራንስፖርት ሚኒስቴርን የ2013 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈጻጸም በገመገመበት ወቅት ነው፡፡

በዲዛይን ለውጥ፣ በወሰን ማስከበር፣ በተቋራጮች አቅም ውስንነትና ክትትልና ድጋፍ  ማነስ ምክንያት የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት እና ከተሽከርካሪና አሽከርካሪ ፍቃድ አሰጣጥ ጋር ያለውን ህገ-ወጥነት ለመቀነስ ሚ/ር መ/ቤቱ ምን አቅጣጫ አስቀምጧ የሚሉት ጥያቄዎች ተነስተው በተቋሙ ሃላፊዎች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

ሚ/ር መ/ቤቱ ከፍተኛ በጀት ወጥቶ የሚሰሩ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ለመጠገን የሚወጣው በጀት ከፍተኛ በመሆኑ ለመንገዶች ፈንድ ባለስልጣን የሚበጀተው በጀትም ይህንን ታሳቢ ያደረገ መሆን እንዳለበት ቋሚ ኮሚቴው አመላክቷል፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሀገሪቱን የገቢና የወጪ ጭነት አሰራር ዘመናዊ በማድረግና የአገልግሎቱን ስርዓት በማቀላጠፍ እንዲሁም የወደብ አማራጮችን በማስፋት ከጅቡቲ በተጨማሪ የታጁራ፣ በርበራን እና የሱዳን ወደብን በመጠቀም አማካይ የመርከቦች የወደብ ላይ ቆይታ ባለፈው አመት ከነበረበት 24 ቀናት 12 ቀናት በመቀነስ በዚህም በአጠቃላይ ባለፉት 9 ወራት ከ559 ሚሊዮን ብር በላይ የሎጀስቲክስ ወጪን ማስቀረት መቻሉን ቋሚ ኮሚቴው በጥንካሬ ገምግሟል፡፡

የትራንስፖርት ኒስቴር ሚኒስት ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ በበኩላቸው የተሽከርካሪና አሽከርካ ፍቃድ አሰጣጥን በተመለከተ በጥናት በመለየት ህገ ወጥነት ላይ በተሳተፉት አካላት ላይ እርምጃ መሰዱንና ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ድጋፍ እየተሰጠ መሆኑንና ከትራፊክ አደጋ ጋር ተያይዞ በበጀት ዓመቱ በተሰራው ስራ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሞት አደጋው እየቀነሰ መምጣቱን ነው የገለጹት፡፡ 

የኢትዮጵያ የመንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ በበኩላቸው ዘርፉ በባህሪው ውስብስብ በመሆኑ ችግሮችን በጥናት በመለየት ለመፍታት እየተሰራ እንደሚገኝ አስታውሰው ባለስልጣን መ/ቤቱ ከ200 በላይ ፕሮጀክቶች እየመራ በመሆኑ ከፍተኛ ጫና እንዳለበትና ከተጀመሩት ፕሮጀክቶች 61 አንዱ ችግር ላይ ያሉና 24 ደግሞ ከጸጥታ ጋር በተያያዘዘ የተስተጓጎሉ መሆናቸውን ጨምረው አብራርተዋል፡፡

የትራንስፖርት ሚ/ር ኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ እንዳሉት ከቅንጅታዊ ስራ አንጻር ከክልል አመራሮችና ባለ ድርሻ አካላት ጋር መግባባት ላይ የተደረሰ በመሆኑ ስራዎች ላይ ለውጦች እየመጡ ቢሆንም በተለይ ከመንገዶች ግንባታ አፈጻጸም መጓተት ጋር ተያይዞ በቅድመ ግንባታ እና በግንባታ ወቅት ያለው ጫና ከፍተኛ መሆኑን እና ለወሰን ማስከበር ብቻ የሚወጣው ወጪ እየጨመረ መጥቶ ከ10 ቢሊዮን በላይ መድረሱን አንስተዋል፡፡ 

በኢያሱ ማቴዎስ