የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ መልዕክት

የተከበሩ አቶ ታገሠ ጫፎ

በአገራችን የፓርላማ ዴሞክራሲ ስርዓት መተግበር ከጀመረ ከሩብ ምዕተ ዓመት በላይ ተቆጥሯል፤ አራት  የምክር ቤት ዘመናት አልፈው እነሆ በአሁን ወቅት በአምስተኛው ምክር ቤት የስራ ዘመን ላይ እንገኛለን፡፡ ባለፉት ጊዜያት ምክር ቤቱ በህገ መንግስቱ የተሰጡትን ቁልፍ ተግባራት (ህግ ማውጣት፣ ክትትልና ቁጥጥር እና የህዝብ ውክልና ስራ) ከመወጣት ረገድ መሻሻሎች ተስተውለዋል ማለት ይቻላል፡፡

አምስተኛው ምክር ቤት በአምስተኛ ዓመት የስራ ዘመኑ (በ2012 በጀት ዓመት) የመንግስትን ፖሊሲዎች፣ ፕሮግራሞችና እቅዶች ሊያስፈፅሙ የሚችሉ 59 አዋጆችን እና 12 ውሳኔዎችን አፅድቋል፤ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ጋር በአካሄደው የጋራ ጉባኤም አራተኛውን የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ለሶስተኛ ጊዜ እንዲራዘም ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

አገራዊ ሰላምንና ደህንነትን ማስቀጠል የወቅቱ የመንግስት ቁልፍ አንገብጋቢ ጉዳይ እንደመሆኑ ከዚህ አንፃር የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር፣ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር እና የጥላቻ ንግግር እና ሃሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ምክር ቤቱ በህግ አወጣጥ ሂደት ካፀደቃቸው አዋጆች መካካል ናቸው፡፡

ኮቪድ-19 ወረርሽኝ በሳደረው አሉታዊ ተፅዕኖ ሳቢያ የክትትልና ቁጥጥር ስራን በሚፈለገው አግባብ ሙሉ በሙሉ ማስኬድ ባይቻልም የአንዳንድ ተቋማትን የእቅድ አፈፃፀም እና ታላቁ የህዳሴ ግድብን ጨምሮ በተመረጡ ግዙፍ ፕሮጀክቶች የመስክ ጉብኝት በማካሄድ ያሉበትን የአፈፃፀም ደረጃ ለመገምገም ተችሏል፡፡

የሕዝብ ውክልና ስራን በተመለከተም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ፍላጎት መሰረት ያደረጉ ውይይቶችንና ክርክሮችን ተካሂደዋል፡፡ ከመቸውም ጊዜ በላይ የምክር ቤቱ አባላት የሕዝብንና የአገርን ጥቅም ማዕከል ያደረጉ ጥያቄዎችን በማንሳት ሃሳባቸውን በነፃነት ያንፀባረቁበት የምክር ቤት ዘመን በመሆኑ ልዩ የሚያደርገው ሲሆን ይህም ለአገራችን የፓርላማ ዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የራሱን አሻራ ጥሎ እንደሚያልፍ የሚታመን ነው፡፡

በፓርላማ ዲፕሎማሲው ዘርፍ ምክር ቤቱ በሚያካሂዳቸው በሁለትዮሽና በባለብዙግ ንኙነቶች የአገር ገፅታን፣ ክብርና ጥቅም ከፍ የሚያደርጉ ስራዎችን ለመስራት ተሞክሯል፡፡ በተለይ ምክር ቤቱ በሚሳተፍባቸው የባለብዙ መድረኮች ላይ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ስለታላቁ የህዳሴ ግድባችን ፕሮጀክት ትክክለኛ መረጃ እንዲይዝ ለማድረግ የፕሮጀክቱ አላማ የጋራ ጥቅምና የፍትሀዊ ተጠቃሚነት መርህን የተከተለ መሆኑ፤ ግድቡ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ልማት ብቻም ሳይሆን ለቀጠናው ብሎም ለመላው አፍሪካ ሕዝቦች እጅግ ጠቃሚና አስፈለጊ መሆኑን ለማስረዳት ጥረት ተደርጓል፡፡

በአሁን ወቅት በምክር ቤቱ የሪፎርም አጀንዳዎች ተቀርፀው በሂደት ላይ የሚገኙ ሲሆን የህግ አወጣጥ ሂደቱን ማሻሻል በተመለከተ የህግ አርቃቂ ኮሚሽን ማቋቋም፣ የህግ ረቂቅ ማንዋል ዝግጅት፣ ከደረስንበት የፖለቲካ ለውጥ አንፃር የምክርቤቱን የአሰራር ደንብ ማሻሻል እና የክትትልና ቁጥጥር ማንዋል ዝግጅት ይገኙበታል፡፡

በቀጣዩ ዓመት የክትትልና ቁጥጥር ማንዋሉን ተግባራዊ በማድረግ አስፈፃሚ የመንግስት አካላት የመንግስት እቅዶችን፣ ፖሊሲዎችን፣ ፕሮግራሞችንና ፕሮጀክቶችን ከመፈፀም እና የመንግስትን በጀት ለታለመለት ዓላማ ከማዋል አንፃር የሚገመገሙ እና ስራቸውን ይበልጥ በግልፅነት እና ተጠያቂነት እንዲያከነውኑ ለማድረግ በክትትልና ቁጥጥር ስራው ትኩረት የሚሰጠው ይሆናል፡፡

በመጨረሻም በአገራችን ከሁለት ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ለውጥ በመካሄድ ላይ ይገኛል፤ የፖለቲካ ለውጡን ተከትሎ ተግባራዊ እየሆኑ ያሉ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ የሪፎርም ስራዎች በአገራችን እውነተኛ የዴሞክራሲ ስርዓት እንዲገነባ፣ ማህበራዊ ፍትህና የዜጎች እኩልነት የተረጋገጠባት የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ተስፋ ሰጪ እርምጃዎች ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር በዓለም መድረክ በዲፕሎማሲው መስክ የመደራደር አቅማችንን በማሳደግ የአገራችንን ክብርና ጥቅም በማስጠበቅ የህዳሴውን ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት ማጠናቀቃችን የኢትዮጵያ የብልፅግና ጉዞ ለአፍታም ያህል የማያጠራጥር መሆን አንዱ ማሳያ ነው፡፡

በሌላ በኩል የሰላም፣ የደህንነትና የኢኮኖሚ ልማት ጉዟችንን ለማደናቀፍና ወደ ኋላ ሊጎትቱን የሚሞክሩ፤ ከባህላዊ እሴቶቻችን ያፈነገጡ ተግባራት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንድነታችንን ለመሸርሸር እየተፈታተኑን ይገኛሉ፡፡ እኛ ኢትዮጵያዊያን ከዋና የልማት አጀንዳዎቻችን የሚያዘናጉን ለእንደነዚህ ዓይነቶች እኩይ እሳቤዎችና ተግባራት ቦታ ሳንሰጥ በአንድነት ቆመን ወደ ፊት ለልማትና ብልፅግና መገስገስ ይኖርብናል፡፡

የጀመርነውን የልማትና የእድገት ጉዞ እውን መሆን ከጀመርናቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱና ዋነኛው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ነው ፤ ሁላችንም ኢትዮጵያዊያን ከሊቅ እስከ ደቂቅ  አንድነታችንን በትግባር ያሳየንበትን ይህን ግድብ በአንድ ላይ ሆነን በተባበረ ክንድ እንደቆምነው ሁሉ በተባበረ ክንድ ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ የጀመርነውን ድጋፍ አጠናክረን እንድንቀጥል በዚህ አጋጣሚ በእኔና በምክር ቤቱ ስም መልእክት ማሳተላለፍ እወዳለሁ፤ አዲሱ አመት ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሰላም፣ የአንድነትና የብልፅግና እንዲሆን እመኛለሁ፡፡

አመሰግናለሁ፡፡