(ዜና ፓርላማ)፤ ሐምሌ 22፣ 2014 ዓ.ም.፤ አዲስ አበባ፤ የኢትዮጵያ እና አዘርበይጃን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል፤ በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመላከተ፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ዲማ ኖጎ (ዶ/ር) የአዘርበይጃንን የዲፕሎማቲክ ልዑክ በዛሬው ዕለት ተቀብለው ባወያዩበት ወቅት፤ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ለዘመናት የቆዬ ታሪካዊ ትስስር እንዳለው ተናግረዋል፡፡

የተከበሩ ሰብሳቢ አክለውም፤ ሁለቱ ሀገራት በፓርላማ ዲፕሎማሲ፣ በትምህርት ዘርፍ እንዲሁም በሕዝብ ለሕዝብ የጀመሩትን ግንኙነት በይበልጥ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው፣ የፓርላማው ፍላጎት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አዘርበይጃን በትምህርት እና በንግዱ ዘርፍ ካላት ልምድ እና ተሞክሮ በመነሳት ለሀገራችን የምታበረክተውን አስተዋጽዖ አጠናክራ እንድትቀጥል የጠየቁት ሰብሳቢው፤ የአዘርበይጃን ባለሀብቶችም ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ኢንቨስት ቢያደርጉ ውጤታማ እንደሚሆኑም አያይዘው ገልጸዋል፡፡

የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል የተከበሩ አምባሳደር ቶፊክ አብዱላሂ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረውን የሁለቱን ሀገራት የፓርላማ ዲፕሎማሲ በይበልጥ ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል።

በቀጣይ በትምህርት፣ በኢንቨስትመንት፣ በንግዱ ዘርፍ እና በሌሎችም መስኮች ተባብሮ በመሥራት፤ የሁለቱን ሀገራት ወንድማማችነት እና የምጣኔ-ሀብት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ፣ በትኩረት መሥራት እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል፡፡

በኢትዮጵያ የአዘርበይጃን ሪፐብሊክ ተጠባባቂ አምባሳደር (Charge d'Affaires) እና ዲፕሎማት ሚስተር ሩስላን ናሲቦቭ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ቀደምት የሰው ዘር መገኛ መሆኗን አስታውሰው፤ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት በባሕል፣ በፓርላማ ዲፕሎማሲ እና በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት በይበልጥ ማጠናከር እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

ሚስተር ሩስላን ናሲቦቭ አክለውም፤ በኮቪድ ተቀዛቅዘው የነበሩትን የኢንቨስትመንት እና የንግድ ሥራዎች እንቅስቃሴ በማጠናከር፣ የሁለቱን ሀገራት ዘርፈ-ብዙ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚቻል አስገንዝበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- መኩሪያ ፈንታ

ቀን፡- ሐምሌ 22፣ 2014 ዓ.ም